አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቻይና በተከሰተው የኮሮና ቨይረስ ህይወታቸውን ያጡ እና በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር አሁንም እየጨመረ መሆኑ ታውቋል።
እስከ ዛሬ ድረስ ባለው ሪፖርት መሰረት በኮሮና ቨይረስ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች በቻይና ብቻ 813፤ በፊሊፒንስ እና በሆንግ ኮንግ አንድ፣ አንድ ሞት መመዝገቡ ነው የተገለፀው።
በቻይና ከተመዘገበው ሞት ውስጥ የኮሮና ቨይረስ በተቀሰቀሰባት ሁቤይ ግዛት ብቻ የ780 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፥ ቀሪዎቹ በሌሎቹ የቻይና ክፍሎች ውስጥ የተመዘገበ መሆኑም ታውቋል።
በኮሮና ቨይረስ የተመዘገበው ሞትም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2003 በሳርስ የተከሰተውን 774 ሞት መብለጡም ነው የተነገረው።
በአሁኑ ወቅት በኮሮና ቨይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም ከ34 ሺህ 800 በላይ መድረሱንም ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት።
በተያያዘም የኮሮና ቫይረስ ከቻይና ውጭ በ25 ሀገራት መታየቱን እና በፊሊፒንስ እና በሆንግ ኮንግ የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት።
የዓለም ጤና ድርጅት በሳላፍነው ወር ላይ የኮሮና ቫይረስን የዓለም ጤና ስጋት ነው በሚል ያወጀ ሲሆን፥ ይህን የዓለም የጤና ስጋት የሆነውን ቫይረስ ለመከላከል 675 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እንድሚያስፈልግ መግለጹ ይታወሳል።
ሀገራትም ለዚህ ስራ ትብብር እንዲያደርጉም ጥሪውን አቅርቧል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ