የሀገር ውስጥ ዜና

ደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበርነት ስፍራን ተረከበች

By Tibebu Kebede

February 09, 2020

አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበርነት ስፍራን ተረከበች።

ዛሬ በተጀመረው 33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች መደበኛ ጉባኤ ላይ ነው ደቡብ አፍሪካ የፈረንጆቹ 2020 የህብረቱ የወቅቱ ሊቀመንበርነትን ስፍራ የተረከበችው።

የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳም ከግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ ኤልሲሲ ሊቀመንበርነቱን ተረክበዋል።

ፕሬዚዳንት ራማፎሳ የሊቀመንበርነት ሀላፊነቱን ከተረከቡ በኋላ ባሰሙት ንግግር ደቡብ አፍሪካ እና ደቡብ አፍሪካውያን ይህንን ሀላፊነት በብቃት እንደሚወጡ ቃል ገብትዋል።

የህብረቱ አባል ሀገራትም ለዚህ ሀላፊነት ስኬት ድጋፋቸውን እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይም በ2063 አጀንዳን ለማሳከት የተጀመሩ ስራዎችን በማስቀጠል አህጉሪቱ የሚያስፈልጋትን የኢኮኖሚ ብልፅግና ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በተለይም በአባል ሀገራቱ መካከል በኢኮኖሚ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲተሳሰሩ መስራት ይገኝበታል።

ሴቶችን በማብቃት እና በስራ እድል ፈጠራ ተጠቃሚ ማድረግ፣ በመልካም አስተዳደር እና ዴሞክራሲ አጀንዳ ላይ ትኩረት ሰጥታ ትሰራለች ብለዋል።

ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ መፈለግ በሚል መርህ በአህጉሪቱ ላሉ ግጭቶች መፍትሄ መፈለግም ደቡብ አፍሪካ በሊቀመንበርነት ቆይታዋ ትኩረት ሰጥታ የምታከናውነው ይሆናልም ነው ያሉት።

ደቡብ አፍሪካ የህብረቱ የወቅቱን ሊቀመንበርነት ሀላፊነት ስትረከብ የዘንድሮው ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

ሀገሪቱ ከ18 ዓመት በፊት በቀድሞ ፕሬዚዳንት ታቦ ሚቤኪ የስልጣን ዘመን ህብረቱን በሊቀመንበርነት መርታለች።