አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 19 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የጂቡቲ ወደቦችና ነጻ ቀጠና ባለስልጣን የወደብ-አየር የጭነት አገልግሎትን በይፋ አስጀመሩ።
አገልግሎቱ ላይ የጂቡቲ ወደቦች እና ነጻ ቀጠና ባለስልጣን ሊቀ መንበር አቡበክር ኦማር ሃዲ፣ በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አካባቢያዊ ሃላፊ እና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት ነው በይፋ የተጀመረው።
በዚህ ወቅትም ከቻይና ሼንዘን የተጫነና መዳረሻውን ናይጀሪያ ሌጎስ እና ካኖ ከተሞች ያደረገ 17 ቶን ጭነትን አየር መንገዱ ከጂቡቲ ወደብ በማጓጓዝ አገልግሎቱን ጀምሯል።
የአገልግሎቱ መጀመር አየር መንገዱ በጭነት አገልግሎት የሚሰጠውን አገልግሎት በእጥፍ ለማሳደግ ይረዳዋል ተብሏል።
ከዚህ ባለፈም ጂቡቲን የወደብ- አየር የጭነት አገልግሎት ማዕከል እንድትሆን ያደርጋታል መባሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
የወደብ – አየር የጭነት አገልግሎት ከባህር እና ከአየር የተናጠል የጭነት አገልግሎት በተሻለ ፈጣንና ርካሽ መሆኑ ይነገራል።
ይህን መሰሉ አገልግሎት የሁለቱን ሃገራት ግንኙነትና የንግድ ትስስር ከማጠናከር ባለፈ፥ በአፍሪካ እና እስያ መካከል ያለውን ትስስርና ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ ይረዳልም ነው የተባለው።
ትናንት ይፋ በሆነው በዚህ የወደብ – አየር የጭነት አገልግሎት፥ አየር መንገዱ በጂቡቲ ወደብ የሚከማቹ ሸቀጦችን ያጓጉዛል።
ይህም ለአየር መንገዱ ተጨማሪ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችልና አቅሙን የሚያጠናክርበት እንደሚሆን ታምኖበታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!