የሀገር ውስጥ ዜና

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ ከካናዳ አቻቸው ጋር ተወያዩ

By Tibebu Kebede

February 08, 2020

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ጋር ዛሬ በፅህፈት ቤታቸው ተወያዩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ትናንት ምሽት ነበር ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ የገቡት።

ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤትም ሁለቱ መሪዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

በዚህም ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የኢትዮጵያ እና ካናዳ ግኑኝነት እጅግ የጠነከረ መሆኑን አንስተዋል።

ለሀገራቱ ግኑኝነት ኢትዮጵያ ትልቅ ቦታ ትሰጣለችም ብለዋል።

ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የዘለቀው ይህ የሁለቱ ሀገራት ግኑኝነት ይበልጥ እንዲጠናከርም ኢትዮጵያ በብርቱው ትፈልጋለቸም ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በዴሞክራታይዜሽን እና ሁለተናዊ ብልጽግናን በመገንባት ላይ ስለተመሠረቱት ባለብዙ ገጽታ ቀጣይ የሪፎርም ሥራዎች ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ካናዳ በትምህርት ዘርፍ፣ በልማት እና በኢኮኖሚ ትብብር ረዥም ዓመታትን ያስቆጠረ ግኑኝነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ካናዳ አሁንም ይህን ግኑኝነት የበለጠ የማጎልበት ፍላጎት እንዳላት ገልፀዋል።

አክለውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ኢትዮጵያ የተሻለ ተስፋ እንዲኖራት አድርገዋልም ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚካሄዱትን ለውጦች እና ሪፎርሞች እንደሚያደንቁና እንደ ወዳጅ፣ ደግሞም እንደ አጋር በጎን ሆነው ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

ሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች የጋራ ፍላጎት በሚስተዋልባቸው የልማት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ንግድ፣ የኢነርጂ ኢንቨስትመንት፣ አግሮ-ፕሮሰሲንግ፣ መድኃኒት እና ተያያዥ ግብአቶች ላይ በጋራ ስለመሥራት ተወያይተዋል።

የቀጣናው ሰላምና ደህንነት ላይ በጋራ መሥራትንም አንዱ የትብብር አቅጣጫ አድርገው አንስተዋል።

ሁለቱ መሪዎች ከውይይታቸው በኋላ የአንድነት ፓርክን በጋራ ጎብኝተዋል።

 

በአልአዛር ታደለ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ! https://t.me/fanatelevision