የሀገር ውስጥ ዜና

በደቡብ ክልል በአንደኛው ሩብ ዓመት 4ሺህ 800 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል

By Meseret Awoke

October 23, 2021

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) በክልሉ በሩብ ዓመቱ ከ8 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማቅረብ እቅድ ቢያዝም የቀረበው 4ሺህ 800 ቶን ቡና መሆኑ ተገለጸ።

የክልሉ ቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሬድዋን ከድር ÷ በዘንድሮ ዓመት በክልሉ የቡናን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከቡና ምርት 1ነጥብ 2 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ በ2013 ዓ.ም ከቡና ምርት 907 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር የተገኘ ሲሆን÷ በ2014 ከቡና ምርት 1ነጥብ2 ቢሊየን ዶላር የወጭ ምንዛሪ ለማግኘት መታቀዱ ተገልጿል።

የደቡብ ክልል ቡና ጥራትና ቁጥጥር ግብረ ሀይል በክልሉ የቡና ምርትን ለማሳደግ በዘርፉ ያጋጠሙ ችግሮችን እየገመገመ ሲሆን÷ በ2013 የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ክልሉ ለሀገር ማበርከት ካለበት አበርክቶ ያነሰ ነውም ብለዋል አቶ ሬድዋን።

ጌዲኦና ወላይታ ዞኖች እንዲሁም አማሮ ልዪ ወረዳ መልካም አፈፃፀም ያሳዩ መሆናቸውን ገልጸው÷ ሆኖም ወልቂጤ ከተማ የቡና ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በጉልህ የሚታይበትና አብዛኛው የክልሉ የቡና ምርትም በህገወጥ መንገድ በዚህ በኩል አልፎ ለሀገር ጥቅም እያሳጣ በመሆኑ ጠንካራ ቁጥጥር ያስፈልጋል ብለዋል።

የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ባለፈው ዓመት የተሰራው ስራ መልካም መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ÷ በቂ ቅድመዝግጅት አድርጎ አለመስራት፣ የቡና አምራች አርሶ አደሮችና ነጋዴዎች መካከል ጠንካራ ግንኙነቶች አለመኖሩን አንስተዋል።

ይህም የቡና ብክነትን ማስከተሉ፣ ሌብነት፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ህጋዊ የቡና አቅራቢዎችን መፍጠር አለመቻል ትልቁ ችግር እንደነበር ጠቅሰው÷ በዚህ ዓመት እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ሁሉም ርብርብ ማድረግ አለበት ብለዋል።

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ተስፋዬ ይገዙ የክልሉ መንግስት የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆኑን አንስተው ÷ ክልሉ ካለው የቡና አቅም አንፃር ግን ብዙ ይቀረናል ነው ያሉት።

በዚህ ዓመት ህገወጥ የቡና ንግድን ለመቀነስ በትኩረት እንሰራለን ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ÷ ሁሉም የመንግስት አካል ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ህገወጥነትን አጥብቆ መከላከል እንዳለበት ገልጸዋል።

በጥላሁን ይልማ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!