Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አሜሪካዊው ምሁር የመንግስታቱ ድርጅትና አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጽሙትን ሴራ አጋለጡ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና አሜሪካ በውስጥ ጉዳይዋ ላይ የሚያሳዩትን ጣልቃ ገብነትና አድሎ በመረጃ መመከት እና ማጋለጥ እንደሚገባት አሜሪካዊው የፖለቲካ ተንታኝና ጋዜጠኛ አንድሪው ኮርይብኮ ጠቁመዋል፡፡
 
ተንታኙ “የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የፈጸሟቸው ሦስት ቅሌቶች” በሚል ባሰፈሩት ተንታኝ ጽሑፍ÷ ተመድ እና አሜሪካ በመንግስታቱ ድርጅት ሙሰኛ ሰራተኞች አማካይነት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ጫና ለማሳደር እያከናወኑት ያለውን ድብቅ ሴራ አጋልጠዋል፡፡
 
ለአብነትም የሰብዓዊ እርዳታ ጭነው ትግራይ ክልል የገቡ የዓለም ምግብ ድርጅት 428 ተሽከርካሪዎች ሳይመለሱ ስለመቅረታቸው ተመድም ሆነ አሜሪካ ምንም ዓይነት መረጃና ምላሽ ከመስጠት መቆጠባቸውን ያነሳሉ፡፡
 
እነዚህን ተሽከርካሪዎች አሁን ላይ አሸባሪው ቡድን ህወሓት ታጣቂዎቹን ወደ ጦር ሜዳ አስገብቶ በግልጽ እየተጠቀማቸው መሆኑን ለመናገር እንዳልደፈሩም ጠቅሰዋል፡፡
 
በተገላብጦሹ የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሰብዓዊ አቅርቦት እንዳይደርስ መተላለፊያ መንገዶቸን ዘግቷል የሚል መሰረተ ቢስ ክስ ላይ መጠመዱን ነው የገለጹት፡፡
 
ይህም የመንግስታቱ ድርጅት እና አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት ባለፈ መንግስት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳት እንዲደርስ እያደረገ ያለውን ጥረት ለማጠልሸት ብሎም እውቅና ላለመስጠት የሚያደርጉት ሴራ መሆኑን ያትታሉ፡፡
 
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ የተሰማሩ የመንግስታቱ ድርጅት 7 ሙሰኛ ሰራተኞች ከተሰጣቸው የሥራ ሃላፊነት ውጪ ለሽብር ቡድኑ ድጋፍ ሲሰጡ በመገኘታቸው ከሀገር እንዲወጡ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡
 
ይሁን እንጂ የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት ሰራተኞቹ የፈጸሙትን ያልተገባ ስራ ማጣራት እና ቅጣት ማስተላለፍ እንዲሁም በሌሎች ታማኝ ሰራተኞች መተካት ሲገባው÷ አይኑን በጨው አጥቦ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ አላስፈላጊ ጫና ለማሳደር ታትሮ እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
 
በተጨማሪም በኢትዮጵያ የተመድ የስደተኞች ድርጅት ኃላፊን ጨምሮ ሌሎች ሰራተኞች አፈትልኮ ወጣ በተባለው ሚስጢራዊ የድምፅ ቅጂ የመጋረጃ ጀርባ ስራው የተጋለጠበት ድርጅቱ፥ሃላፊዎቹን በእረፍት ስም ወደ አሜሪካ እንዲመለሱ ማድረጉ ሌላኛው የሴራው ማሳያ መሆኑን ያብራራሉ፡፡
 
ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግሥትና እና ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የሀገሪቱ ዜጎች አሜሪካ እና አጋሮቿ እንዲሁም የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት ሰራተኞች በሀገር የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚያሳዩትን አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት በማስረጃ ማጋለጥ፤ ለዚህም በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸው ነው አንድሪው ኮርይብኮ ያሳሰቡት፡፡
 
ከዚህ ባለፈም የኢትዮጵያ መንግስት ምክንያታዊ ሃሳብ በሚያራምዱ እና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ከሚያከብሩ አጋር ሀገራት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ በቅንጅት መስራት እንዳለበት ምክር ሃሳብ አቅርበዋል፡፡
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version