አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አሸባሪው ህወሓት ከሰሞኑ በሁሉም ግምባሮች እጅግ መጠነ ሰፊ የማጥቃት ዘመቻ ከፍቷል ብለዋል፡፡
በከፈተው ጥቃት በተለይም በሰሜን ወሎ እና በአፋር ጭፍራ ላይ ንጹሃን ላይ ጥቃት አድርሷል፡፡
ከባድ የጦር መሳሪያዎችን እስከ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ በመተኮስ ከ30 የማያንሱ ንጹሃንን መግደሉንም አስታውቀዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ የማጥቃት ዘመቻ በዋነኛነት ወታደራዊ ኢላማዎችን ማዕከል ያደረገ ሳይሆን ህጻናትን÷ ሴቶችን፣ አዛውንቶችን፣ የጦር ጉዳተኞችን እና ሽማግሌዎችን በመጠቀም ብዙ ሺህ ሲቪሎችን ያሳለፈ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ጁንታው ሶስት የውጊያ ረድፍ የያዘ ሲሆን የመጀመሪያ ረድፍ በሺዎች የሚቆጠሩ የተደራጀ የጦር መሳሪያ ያልያዙ ሲቪሎች፣ ሁለተኛው ረድፍ ክላሽ ዕና የቡድን መሳሪያ የታጠቁ ታጣቂዎች ሲሆኑ÷ ሶስተኛው ረድፍ መካናይዝድ ጦር ነው፡፡
ከፊት ያሰለፏቸው ሀይሎች አብዛኛዎቹ ከጦር መሳሪያ ይልቅ የግብርና መሳሪዎችን የያዙ እና የደረሱ ሰብሎችን አጭዶ ዘርፎ ለመውሰድ አላማ ያደረጉ ናቸው፡፡
ይህንን አላማቸውን ለማሳካት እና ኢትዮጵያን ለማፍረስ አሸባሪው ህወሓት በሁሉም ግምባሮች ውጊያ ከፍቷል፡፡
ይህንም ለመመከት ታዲያ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲረባረብ ተጠይቋል፡፡
ጦርነቱ ባለበት ቀጣና ያለ ሁሉም ወጣት፣ ሴት፣ ጎልማሳ እና ማንኛውም ጉልበት ያለው ሁሉ ከጀግናው መከላከያ ሃይላችንና ከልዩ ሃይሎች ጎን በመሰለፍ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳውን አሸባሪ ቡድን መመከት የግድ ይለዋል ብለዋል፡፡
በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ኢትዮጵያውያንም የደረሱ ሰብሎችን ያለ ብክነት ቶሎ በመሰብሰብ ለቀጣይ የመስኖ እርሻ መዘጋጀት አለባቸው ተብሏል፡፡
ሁሉም የመግስት ሰራተኛም የተሰጠውን ሃላፊነት በእጥፍ መወጣት አለበትም ብለዋል፡፡
የንግዱ ማህበረሰብም በትክክል እና በትጋት የመስራት ግዴታውን እንዲወጣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በመግለጫው አስታውቋል፡፡
በአልዓዛር ታደለ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!