አዲስ አበበ፣ ጥቅምት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 1ሺህ 496 ኛው የመውሊድ በዓል፣ በታሪካዊው የቶንገላ አብዱሰላም መስጂድ፣ የአካባቢው ህዝበ ሙስሊም ምዕመናን ከተለያዩ አካባቢዎች ከመጡሙስሊም ምዕመናን እንግዶች ጋር በመሆን አከበሩ፡፡
የቶንጎላ አብዱሰላም መስጂድ÷ በከፋ ዞን የሚገኝ ሲሆን፣ በ14ኛው ክፍለ ዘመን እንደተመሠረተና ከ7 መቶ በላይ ዓመታት እንዳስቆጠረ ይነገራል።
የመስጂዱ መስራች፣ አብዱሰላም ቢን ሐጂ ሱሌይማን÷ ወደ አካባቢው ሲመጡ የእስልምና እምነት በአካባቢው እንዳልተጀመረም የሚነገር ሲሆን፣ አብዱሰላም ቢን ሃጂ ሱለይማን ወደ አካባቢው መጥተው በማስተማር እስልምናን በአካባቢው እንዳስፋፉ ይነገርላቸዋል፡፡
በወቅቱም ከእምነት ማስፋፋት ባሻገር ከከፋ ንጉስ ጋርም ጥሩ ግንኙነት እንደነበራቸው ይነገራል፤ ከዚህም የተነሳ ቲፋ በሚባል አካባቢ ቦታ ተሰጥቷቸው በመሥራት ለአካባቢው ጠንካራ የስራ ተምሳሌት መሆን እንደቻሉ ከታሪካቸው ጋር አብሮ ይነሳል፡፡
ቶንገላ አብዱሰላም መስጂድ÷ የሚከበረውን በዓል ለየት የሚያደርገው፣ ጸሎት(ዱአ) የሚደረገው በሦስት ቋንቋዎች መሆኑ ነው፡፡ አረብኛ፣ አማርኛ እና ከፍኛ ቋንቋዎች በመስጂዱ ውስጥ ጸሎት(ዱአ) ለማድረግ ጥቅም ላይ እንደሚውሉም ተመላክቷል፡፡
ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ምዕመናንም መውሊድን በከፍተኛ ጉጉት እና ናፍቆት እንደሚጠብቁት የተናገሩ ሲሆን፣ በስፍራው የተደረገ ዱአ ያሰቡትን ያሳካል፣ ክፉ ያደረገውንም ይቀጣል፣ ተብሎ ስለሚታመን በዚህ ዓመትም በሚከበረው የመውሊድ በዓል ላይ ለመታደም እና በረከቱን ለመቋደስ መምጣታቸውን ነው የተናገሩት፡፡
የአካባቢው ሙስሊሙ ማህበረሰብም በዓሉን ከወንድሞቹ የክርስትና እምነት ተከታዮች ጋር አክብረውታል፡፡
በፍሬው ዓለማየሁ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!