የሀገር ውስጥ ዜና

የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንደምትደግፍ ተገለጸ

By Tibebu Kebede

February 07, 2020

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የሚደረገውን እንቅስቀሴ እንደምትደግፍ ተገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋችው ከተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዲኤታ ረይም አል ሃሽሚ ጋር ተወያይተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ እና የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ያላቸው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፥ ግንኙነቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል ኢትዮጵያ ከመቸውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ ናት ብለዋል።

የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች የኢትዮጵያን አጠቃላይ ማሻሻያ በመደገፍ እያደረገች ላለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍና በሀገሪቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስለሚደረግላቸው ድጋፍም ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ ትኩረት በተሰጣቸው ዘርፎች ዙሪያ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፥ የሃገሪቱ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች በስፋት እንዲሳተፉም ጠይቀዋል።

የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዲኤታ ረይም አል ሃሽሚ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ በመከናወን ላይ ባለው ማሻሻያ ሃገራቸው ደስተኛ መሆኗን በመጥቀስ ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ሃገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በበርካታ ጉዳዮች በትብብር እየሰራች መሆኗን በመጥቀስም፥ ይህን ግንኙነት በባህል፣ በግብርና፣ በቱሪዝም እና በሌሎች ዘርፎች ይበልጥ ለማጠናከር እየሰራች መሆኗንም አንስተዋል።

አያይዘውም የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ ቀንድ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ጠቁመው፥ የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን በሚደረገው እንቅስቃሴ ሙሉ ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።

በተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች የሚኖሩ ከ150 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ባህላቸውን እና እምነታቸውን ለሌላው ዓለም ማስተዋወቅ እንዲችሉም አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ ነው ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ! https://t.me/fanatelevision