አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 1 ሺህ 496ኛው የነብዩ ሙሐመድ ልደት (መውሊድ) በዓል አከባበር በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዳንግላ ከተማ በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች እና የህልውና ዘመቻውን በመደገፍ ተከብሯል፡፡
የከተማው ነዋሪ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለህልውና ዘመቻው ድጋፍ አድርገዋል ሲል አሚኮ ዘግቧል፡፡
የዳንግላ ወረዳ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሐሰን ኢብራሂም ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ዘረኝነትን የሚጸየፉ፣ ለፍትሕ፣ ለእኩልነትና ለአንድነት ዘብ የቆሙ ናቸው ብለዋል፡፡
ሕዝበ ሙስሊሙም የእርሳቸውን አስተምህሮ መከተል እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አሸባሪው የትህነግ ቡድን ሥራ በእስልምና ሃይማኖታዊ አስተምህሮ የሚወገዝና ከኢትዮጵያ ታሪክ ያፈነገጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሕዝበ ሙስሊሙም ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በመሆን ሽብርተኛው ትህነግ የከፈተውን ጦርነት በጽናት ሊመክተው ይገባል ብለዋል፡፡
1 ሺህ 496ኛው የመውሊድ በዓል ሲከበርም÷ ለፀጥታ ኃይሉ ደጀን በመሆን፣ ዘማች ቤተሰቦችን፣ የታመሙትን፣ ወላጅ የሌላቸው ሕፃናትንና አቅመ ደካሞች በማገዝና በመጠየቅ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!