Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ትዊተር በሶስት ወራት 1 ቢሊየን ዶላር ገቢ ሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ትዊተር በ2019 አራተኛ ሩብ ዓመት ከተጠበቀው በላይ 1 ቢሊየን ዶላር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።

ይህም በሩብ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ያስመዘገበው ከፍተኛ የገንዘብ መጠን መሆኑ ተጠቁሟል።

ገቢው የተሰበሰበው ኩባንያው ፖለቲካ ነክ ማስታወቂያዎችን አግዶ መሆኑ የኩባንያው ገቢ እያደገ መምጣቱን አመላካች ነው ተብሏል።

ኩባንያው በርካታ ደንበኞችን እየሳበ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፥ በአራተኛ ሩብ ዓመት በየቀኑ የሚጠቀሙ እና ማስታወቂያ የሚመለከቱ ደንበኞቹ 152 ሚሊየን ደርሰዋል ነው የተባለው።

የኩባንያው የፋይናንስ ሃላፊ ኔድ ሴጋል አራተኛው ሩብ ዓመት የዓመቱ ጠንካራ ማጠቃለያ መሆኑን ገልጸው፥ የአገልግሎት አሰጣጡ መሻሻል የደንበኞቹን ቁጥር ከፍ እንዳደረገው ተናግረዋል።

የትዊተር ዋና ስራ አስፈጻሚ ጃክ ዶርሴይ በበኩላቸው፥ ለአዲስ ተጠቃሚዎች የሚሆን የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ኩባንያው መስራቱን ገልፀዋል።

ሰዎችን ወዳልተገባ መንገድ የሚመሩ መረጃዎች ትልቁ ችግር መሆኑን በመግለፅ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫቸው እንደሆነም አመላክተዋል።

ምንጭ÷ cnet.com

Exit mobile version