አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችሉ ስራዎች በልዩ ትኩረት የሚከናወኑ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፥ የሁለቱ ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎችንና ሚኒስትሮችን ያካተተ ልኡክ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የግብርና ምርት እየጎበኙ ይገኛሉ።
በጉብኝቱ በኩታ ገጠም የተዘራ ስንዴ፣ በቆሎና ጤፍ፣ የተሻሻሉ የኦቮካዶና ፓፓያ እንዲሁም የቦሎቄ ምርቶችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
አቶ ደመቀ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፥ በኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችሉ ስራዎች ከየትኛውም ጊዜ በላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል።
”ጠንካራ ኢኮኖሚ የገነባ አገር አንድነቱንና ብዝሃነቱን ጠብቆ ይሄዳል፣ ማንም የሚነቀንቀው እና የሚያንገዳግደው አይሆንም” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በአባቶቹ ትጋትና መስዋዕትነት የወረሰው የነጻነት እሴት ተቀባይነት እንዲኖረው የተሻለ ኢኮኖሚ መገንባት የግድ ይላልም ነው ያሉት።
ለዚህ ደግሞ መንግስት ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተሻለ ስራ የሚሰራ ይሆናል ሲሉ አረጋግጠዋል።
በኦሮሚያ ክልል በግብርና ዘርፍ እየታየ ያለው ጥሩ ተሞክሮም ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዲሰፋ የሚደረግ ይሆናል ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፥ ክልሉ ለግብርና ልማት ስራ የተለየ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህም ለኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴና ለመስኖ ስራዎች የተለየ ትኩረት ተሰጥቶ የተሻሉ ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን ገልፀዋል።
በክልሉ በየትኛው አካባቢ ምን በተሻለ መልኩ ሊመረት ይችላል የሚለውን በመለየት በምዕራብ፣ በማሃል እና በምስራቅ በሚል ለይተን አስቀምጠናል ብለዋል።
በዚሁ መሰረት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ማስቀረትና የስራ ዕድል ፈጠራ ማዕከል ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የጉብኝቱ ተሳታፊ ሚኒስትሮችም የተመለከቱት የግብርና ልማት ስራ ተስፋ ሰጭና ብዙ መስራት እንደሚቻል ማየታቸውን ይናገራሉ።
በየደረጃው ያለው አመራር መስራት ከቻለ የኢትዮጵያ ገፅታ መቀየር እንደሚቻል አረጋግጠናል ብለዋል።
በመሆኑም ሚኒስትሮቹ ኢትዮጵያን ለመቀየር ከየትኛውም ጊዜ በተሻለ መልኩ በቁርጠኝነት ለመስራት መዘጋጀታቸውን ነው የገለጹት።
የአካባቢው አርሶ አደሮችም በመንግስት በሚደረግላቸው ድጋፍ ሁለንተናዊ መሻሻሎች እያሳዩ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ወቅት የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆኑንና ከራሳቸው አልፈው ሌሎቹንም ቀጥረው እያሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ሆኖም የግብርና ግብዓት አቅርቦት እጥረትና የገበያ ትስስር ችግር መኖሩን ጠቅሰው ችግሩ እንዲፈታላቸው መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!