Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተመራው የግብርና ስራዎች ጉብኝት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተመራው ልዑክ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች ለሁለት ቀናት የያደረገው የግብርና ስራዎች ጉብኝት ተጠናቀቀ።
የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እንዲሁም የሁለቱ የከተማ አስተዳድር ከንቲባዎች የተሳተፉበት ይህ የሁለት ቀናት የግብርና ስራዎች የመስክ ጉብኝት በኦሮሚያ ክልል በአርሲ፣ በምእራብ አርሲ እና በምስራቅ ሸዋ ዞኖች ነው የተካሄደው።
በተለይም በዱግዳ እና አደአ ወረዳዎች የተመረቱ የስንዴ፣ የቦቆሎ፣ የቦለቄ፣ የፓፓየ እና የአቦካዶ ማሳዎች ተጎብኝተዋል።
ጉብኝቱ በኦሮሚያ ክልል እየተከናወኑ ያሉ የግብርና ስራዎችን በመመለከት መልካም ተሞክሮዎችን ለሌሎችም ክልሎች የማካፈል ዓላማ እንዳለው ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር፥ ኢትዮጵያ ያላትን የመልማት አቅም በመጠቀም በምግብ እህል ራስሰችንን መቻል እንደሚገባን አስገንዝበዋል።
ለዚህም የግብአት፣ የብድር እና የገበያ ትስስር ጥያቄዎችን መፍታት እንደሚገባም ተናግረዋል።
በጉብኝቱ የተሳተፉ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችም ተሞክሮውን በማስፋት እንደየ ክልሎቻቸው የመልማት አቅምና ነባራዊ ሁኔታ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፥ ከሁሉም ክልሎች ጋር በቅንጅት በመስራት በከተማዋ የሚታየውን የአቅርቦት ችግር እና የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር የጋራ የስራ ውል ተፈራርመው ወደ ስራ መግባት እንደሚገባ ነው የገለጹት።
በኦሮሚያ ክልል የተደረገው ጉብኝት በቀጣይ በሌሎችም ክልሎችም እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታውቀዋል።
ለይኩን ዓለም
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
Exit mobile version