Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በጋና ከአየር ብክለት ነጻ የሆኑ ተሽከርካሪዎች በአማራጭነት ለገበያ ቀረቡ

“ሶላር ታክሲ ጋና ሊሚትድ” የተሰኘ ኩባንያ የሀገሪቷን የአየር ብክለት ለመቀነስ የሚያስችል ቻይና ሰራሽ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ለገበያ አቀረበ፡፡

ኩባንያው ጀማሪ እንደ መሆኑ ከፈረንጆቹ 2019 ጀምሮ 150 የኤሌክትሪክ ሳይክሎችና ባለ ሦሥት እግር ተሸከርካሪዎች፣ እንዲሁም ከ60 በላይ የኤሌክትሪክ መኪኖች ለገበያ አቅርቦ ጥቅም ላይ ማዋሉ ነው የተገለጸው፡፡

ከቀረቡት ተሸከርካሪዎች ከፊሉ የፀሐይ ታዳሽ ኃይል የሚጠቀሙ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ በኤሌክትሪክ ኃይል ቻርጅ የሚደረጉ ናቸው ተብሏል፡፡

እንደ ኩባንያው የሥራ ሂደት ሥራ አስኪያጅ ዩጂን አምፎንሳህ÷ ጅማሮው መልካም ቢሆንም በአንዳንዶች ግን ዝናብ ሲዘንብ ኤሌክትሪክ ሊይዘን ይችላል እና ባትሪው ቻርጅ ከጨረሰ መንገድ መሃል ቆመን ልንቀር እንችላለን የሚሉ ጥርጣሬዎች ሲንጸባርቁ አስተውለናል ብሏል፡፡

ሥራ አስኪያጁ÷ እንዲህ ያሉ ስጋቶች ደንበኞቻቸው የኤሌክትሪክ መኪናዎቻቸውን አዘውትረው መጠቀም ሲቀጥሉ እና ወጪ ቀናሽ ብሎም ለአየር ንብረት ተስማሚ መሆናቸውን ሲረዱ እየቀነሱ ይመጣሉ ብሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኩባንያው ቢያንስ ለ250 ሰዎች የሥራ ዕድል እንደፈጠረ የተመላከተ ሲሆን፣ ከሠራተኞቹ ውስጥ የኤሌክትሪክ መሀንዲሶችና ሹፌሮች እንደሚገኙበትም ነው የተገለጸው፡፡

በዘርፉ የወጣ የሀገሪቷ መረጃ እንደሚያመለክተው÷ ጋና በዓመት በአማካይ100 ሺህ ያህል ተሸከርካሪዎችን ታስገባለች፤ ከሚገቡት ተሸከርካሪዎች 90 በመቶ ያህሉ በሌላ ሀገራት ጥቅም ላይ የዋሉና ከፍተኛ ጭስ የሚያስወጡ ናቸው ሲል የዘገበው ሲጂቲ ኤን ነው፡፡

በዓለማየሁ ገረመው

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version