አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት በትግራይ በሚገኙ የኤርትራ ስደተኛ ጣቢያዎች የሚያደርስባቸውን ጥቃት ያመለጡ 244 ስደተኞች በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት አስታወቀ።
ለስደተኞች የሚያገለግሉ 40 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ከተማ አቅራቢያ በተቋቋመው ”አለምዋጭ” የስደተኞች ጣቢያ እየተገነቡ እንደሚገኙም አገልግሎቱ ገልጿል።
በስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት የማይጸምሪ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ጊዚያዊ አስተባባሪ አቶ ስንታየሁ በሪሁን ለኢዜአ እንደተናገሩት አዲ-ሃሩሽና ማይ-አይኒ ጊዜያዊ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ይኖሩ የነበሩ 25ሺህ ያህል የኤርትራ ስደተኞች በአሁኑ ወቅት ያሉበት ሁኔታ አይታወቅም።
አሸባሪው ቡድን በመጠለያዎቹ ላይ በፈጸመው ዝርፊያና ወረራ ጉዳት ማድረሱን ጠቁመው÷ ስደተኞችም መበታተናቸውንና አንዳንዶቹም እርዳታው በመቆሙ ለልመና መዳረጋቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ስደተኞቹ የህክምና ድጋፍ እንደማያገኙና አንዳንዶቹም በሽብር ቡድኑ ታፍነው ወዳልታወቀ ሥፍራ ስለመወሰዳቸውም ገልጸዋል።
የሽብር ቡድኑ በሁለቱ መጠለያ ጣቢያዎች መድፎችና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎችን እንደጠመደባቸውና ስደተኞቹንም መሳሪያዎቹን እንዲያጓጉዙ በማስገደድ ላይ እንደሚገኝ አቶ ስንታየሁ አስታውቀዋል።
ከህወሓት የሽብር ቡድን አፈናና ግድያ ያመለጡ 244 ስደተኞችም በዳባት ከተማ በተዘጋጀው ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ እየተስተናገዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይሄንን ችግር ለማቃለልም በሰሜን ጎንደር ዞን የዳባት ወረዳ አስተዳደር በነጻ በተሰጠ 91 ሔክታር መሬት ላይ በተቋቋመው “አለምዋጭ” የኤርትራ የስደተኞች መጠለያ ላይ በ40 ሚሊየን ብር በጀት የጋራ መኖሪያ ቤቶች እየተገነቡ ይገኛሉ።
እያንዳንዳቸው 100 ስደተኞችን እንዲያስተናግዱ ተደርገው እየተገነቡ ካሉት 40 ቤቶች መካከል 15 ያህሉ ግንባታቸው እየተጠናቀቀ መሆኑን አቶ ስንታየሁ አስረድተዋል።
ከስደተኛ መጠለያዎቹ ጎን ለጎንም ለጋራ የምግብ ማብሰያ የሚያገለግሉ ቤቶችና የመጸዳጃ ቤቶች ይሟላሉ ተብሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም እያንዳንዳቸው 25 ሺህ ሊትር የሚይዙ ሦስት የውሃ ታንከሮችም እየተዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ቀደም ሲልም ከአዲ ሃሩሽ፣ ማይአይኒ፣ ህጻጽና ሽመልባ የመጠለያ ጣቢያዎች የመጡ ስድተኞች የተሻለ ደህንነቱ በተረጋገጠ ቦታ መጠለያ እንዲሰራላቸው ሲጠይቁ ቆይተዋል።
በዚህ ዓመት 100 የስደተኛ መጠለያዎችን ለመገንባት ታቅዶ እየተሰራ ነው ያሉት ጊዜያዊ አስተባባሪው÷ 10 ሺህ ስደተኞችንም ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
የአሸባሪው ህወሓት የጥቃት ሰለባ የሆኑት የኤርትራ ስደተኞች አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውሶ ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!