አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) ኢትዮ-ቴሌኮም በሁለተኛ ዙር ማስፋፊያ ስራው በ22 ከተሞች ከፍተኛ ፍጥነት ያለው የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ የኢንተርኔት አገልግሎት ማስጀመሩን አስታወቀ።
ኢዜአ የኩባንያውን መግለጫ ጠቅሶ እንደዘገበው፥ በመጀመሪያው ዙር ከፍተኛ የዳታ አጠቃቀም በሚታይባቸው 92 ከተሞች የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት አስጀምሯል።
በሁለተኛው ዙር የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ አግልግሎት ማስፋፊያ ስራም የዳታ ትራፊክና ፍላጎት መሰረት በማድረግ በ22 ከተሞች አገልግሎት ማስጀመሩን ገልጿል።
ከጥቅምት 2 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በደደር፣ ዱብቲ፣ ደባርቅ፣ እስቴ፣ ሸሃዲ፣ ወረታ፣ ጃዊ፣ አዴት፣ ቢቸና፣ ደጀን፣ ሞጣ፣ አሰላ፣ ጎባ፣ ሮቤ፣ ሶደሬ፣ ባቱ፣ ሃላባ፣ ዱራሜ፣ ኮንሶ፣ ሳውላ፣ ሺንሺቾ፣ እና ወራቤ የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጌያለሁ ብሏል።
በአሁኑ ወቅትም አጠቃላይ 112 ከተሞችን የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ነው ኢትዮ-ቴሌኮም የገለጸው።
ከዚህ ቀደም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ በሆኑት የደሴ፣ ደብረ ታቦር፣ ጎንደር፣ ባህር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ሎጊያ፣ ሆሳአና፣ ሶዶ፣ አርባ ምንጭ እና ቡታጅራ ከተሞችም ተጨማሪ የማስፋፊያ ስራ ተከናውኖ ተግባራዊ መደረጉንም አመላክቷል።
የቴሌኮም አገልግሎት መጠቀሚያ መሳሪያ ወይም ይዘት አቅራቢዎችም በመረጃ የበለጸገ ማህበረሰብና ኢኮኖሚ ለመገንባት በዝርጋታ ላይ የሚገኘውን ከፍተኛ ፍጥነት ያለው የሞባይል ኔትወርክ ግንባታ በማገዝ፥ ለህብረተሰቡ በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!