አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዲሱ አደረጃጀትና የለውጥ ሥራ ዓለም አቀፋዊና ጂኦ ፖለቲካዊ አካባቢያዊ ጉዳዮችን ከግምት ያስገባ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታወቀ።
አደረጃጀቱ ወጪን በመቀነስ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ሥራ ለመሥራት ትኩረት ያደረገ መሆኑም ተገልጿል።
ተቋሙን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የለውጥ ሥራ መከናወኑን÷ በሚኒስቴሩ የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራልና የተቋሙ የለውጥ ሥራ ኮሚቴ አስተባባሪ አክሊሉ ከበደ ገልጸዋል።
የለውጥ ሥራው የታለመለትን ግብ እንዲመታና የተቋሙን ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ የዲፕሎማሲውን ፍኖተ ካርታ የሚያሳይ ዝርዝር ጥናት መካሄዱንም ነው ያብራሩት፡፡
የተቋሙ የለውጥ ሥራዎች በዋናነት በአሰራር፣ በሕግ፣ በአደረጃጀት ማሻሻያና በተቋም ባህል ግንባታ ላይ አተኩሮ ተከናውኗልም ብለዋል፡፡
የለውጥ ሥራው ከአገሪቱ የ10 ዓመት መሪ እቅድ ጋር የተጣጣመና ይህንኑ አገራዊ እቅድ ሊያስፈጽም በሚችል መልኩ በተቋም ደረጃ ታልሞ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።
የተቋሙ የአደረጃጀት ለውጥ ክንውን በዋናነት ተለዋዋጩን ዓለም አቀፋዊና ጂኦ ፖለቲካዊ አካባቢያዊ ጉዳዮችን ከግምት ባስገባ መልኩ መሆኑን ገልጸዋል።
ከሰሜኑ የአገሪቱ አካባቢ ጋር በተያያዘ የመጣውን የውጭ ጫና እና ችግሩን ተከትሎ ሊመጣ የሚችለውን ምጣኔ ሃብታዊ ተግዳሮቶች ለመቋቋም በሚያስችል መልኩ ተካሂዷልም ብለዋል፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ ያስከተለውን ምጣኔ ሃብታዊ ጫና ለመመከትም ከዋና መሥሪያ ቤት ጀምሮ እስከ ሚሲዮኖች ሁሉን አቀፍ አደረጃጀት መሰራቱን ጠቁመዋል።
የአደረጃጀት ማሻሻያው መሥሪያ ቤቱ ተልዕኮውን በብቃት ለመፈጸም፣ ወጪ ለመቀነስና ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጠናከር ያስችላል ብለዋል።
በአደረጃጀቱ መሠረት በአንዳንድ አገራት የተዘጉ ሚሲዮኖች ከዋና መሥሪያ ቤት አልያም ደግሞ መቀመጫቸውን ሌሎች አገራት ባደረጉ ኤምባሲዎች የሚሰሩ ይሆናል።
አዲሱ አደረጃጀት ወጪን በመቀነስ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ሥራ ለመሥራት ትኩረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሥሪያ ቤቱ አዲሱን የለውጥ ሥራ በተመለከተ የተቋሙ ሠራተኞች፣ ዲፕሎማቶችና ተጠሪ ተቋማት ሠራተኞችም ሥልጠና እየወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል።
በተቋሙ የለውጥ ሥራዎችና ግቦች ዙሪያ የጋራ መግባባት ለመፍጠርና ስልጠናው አቅማቸውን ለማጎልበት ያስችላልም ነው ያሉት አቶ አክሊሉ።
የተቋሙን የለውጥ ሥራ ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ የአደረጃጀትና ሌሎች አሰራሮችን ገቢራዊ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!