Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በትግራይ በ44 ተራድኦ ድርጅቶች እስከ ወረዳ ድረስ የሰብዓዊ እርዳታ እየተሰራጨ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል አስፈላጊው የሰብዓዊ እርዳታ በ44 ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች አማካኝነት እስከ ወረዳ ድረስ እየተሰራጨ መሆኑን የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሓን እና ማህበራዊ ትስስር ገጾች ”በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ለተረጂዎች እየደረሰ አይደለም” በሚል የሚያሰራጩት መረጃ የተሳሳተ ነው።

በአንጻሩ መንግስት በትግራይ ክልል ለተረጂዎች የሚሰራጨው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከአጋር ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።

በዚህ መሰረትም ከአዲስ አበባ – መቀሌ የሰብዓዊ እርዳታ ለማጓጓዝ የተፈቀዱ 21 የአውሮፕላን በረራዎች እስከ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ድረስ 21ዱም በራዎች በሰላም ተካሂደዋል ነው ያሉት።

በየብስ በኩልም 686 ሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች በአፋር ክልል ሰመራ በኩል ወደ መቀሌ መጓጓዛቸውን አንስተዋል።

በክልሉ 18 ሺህ 812 ሜትሪክ ቶን የምግብ እና 6 ሺህ 225 ሜትሪክ ቶን ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች መሠራጨታቸውንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በዩኒሴፍ በኩል ከአውሮፖ ህብረት ለሁለተኛ ጊዜ የተለገሱ አልሚ ምግቦች ፣ የድንገተኛ አደጋ የህክምና ቁሳቁሶች እና ሌሎች ግብዓቶች ወደ ክልሉ ተልከዋል።

759 ሺህ 235 ሊትር ነዳጅ ዘይት ወደ መቀሌ መጓጓዙን የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ ተጨማሪ ከ45 ሺህ እስከ 50 ሺህ ሊትር የሚይዙ አስር ነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎችም በቅርቡ መቀሌ መድረሳቸውን ጠቁመዋል።

በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ለሚያሰራጩት እርዳታ ማስፈጸሚያ እና ለአስተዳደር ስራ የሚውል 286 ሚሊየን ብር በላይ ወደ መቀሌ እንዲያጓጉዙ ማረጋገጫ መሠጠቱን ተናግረዋል ።

ይሁን እንጂ አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሓን የራሳቸውን ድብቅ አላማ ለማሳካት እና መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት ለማጠልሸት የሚያሰራጩት የተሳሳተ ዘገባ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በመላኩ ገድፍ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version