አዲስ አበባ፣ጥር 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሰላም ሚኒስቴር የክልሎችን የእርስ በእርስ ግንኙነት ለማጠናከር ባካሄደው የጥናት ግኝት ላይ ውይይት ማካሄዱን አስታወቀ።
የሰላም ሚኒስቴር በክልሎች መካከል ያሉ ችግሮችን በመፍታት ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በጥናት የተደገፉ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን በሚኒስቴሩ የፌደራሊዝም እና የልዩ ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ጀኔራል ፕሮፌሰር ደገፋ ቶሎሳ ተናግረዋል።
የቅድመ ጥናቱ ዓላማ በክልሎች መካከል የትብብር ፎረም ክፍተቶችን በመለየት የመፍትሄ ሀሳቦችን ሰጥቶ ግንኙነታቸውን ማጠናከር መሆኑንም አስረድተዋል።
የሰላም ሚኒስቴር የፌደራሊዚም እና የመንግስታት ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፀጋብርሃን ታደሰ በበኩላቸው፥ ጥናቱ በተጎራባች ክልሎች መካከል ያለው ግንኙነት የሚገኝበትን ደረጃ ለመለየት ታስቦ የተካሄደ ነው ብለዋል።
ይህም የክልሎቹን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ የፀጥታ ዘርፍ፣ የፋይናንስ፣ የትምህርትና የጤና የእርስ በእርስ ግንኙነትን ያካተተ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ጥናቱ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር፣ ትግራይና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች መካከል ያለውን የበይነ መንግስታት ግንኙነት ያለበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ያደረገና ሶስት ቡድኖችን በማዋቀር መካሄዱም ተገልጿል።
የጥናቱ ሪፖርት በውይይት መድረኮች የተሰጡ ተጨማሪ ግብዓቶችን የማጠናከር ስራ ከተሰራ በኋላ ለተጠቃሚዎች ይፋ ይደረጋልም ተብሏል።
በውይይት መድረኩ የፌደራሊዝምና አርብቶ አደር ጉዳዮች ዘርፍ ባለሙያዎችና አመራሮች መሳተፋቸውን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ! https://t.me/fanatelevision