Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሀገር መከላከያ ሰራዊት 14ኛውን የሰንደቅ ዓላማ ቀንን አከበረ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) “በአዲስ ምዕራፍ በተሟላ ሉአላዊነት ለሰንደቅ ዓላማ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል ሃገር መከላከያ ሰራዊት አመራር እና አባላት በተለያዩ ዝግጅቶች እና ስፍራዎች ቀኑን አከበሩ፡፡
በዚህም የምዕራብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ የሠራዊት አባላት፣ የደጀን እግረኛ ክፍለ ጦር፣ የምስራቅ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ፣ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ፣ የኢፌዴሪ የልዩ ዘመቻዎች ኃይል፣ የመከላከያ ጥናትና ምርምር ማዕከል እንዲሁም ጃንሜዳ የሚገኙ የተለያዩ የመከላከያ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡
ሰንደቅ ዓላማ የሀገር መታወቂያ የነጻነት ፣ የብሄራዊ አንድነትና የክብር ምልክት ነው ያሉት የመከላከያ ሚዲያ ዳይሬክተር ብ/ጀነራል ኩማ ሚደቅሳ ናቸው፡፡
14ኛው የብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ጃንሜዳ የሚገኙ የተለያዩ የመከላከያ ክፍሎች በጋራ ባከበሩበት ወቅት ባደረጉት ንግግር÷ ጀግኖች አባቶቻችን ባደረጉት ተጋድሎ የሰንደቅ ዓላማችን ክብር እና ነጻነት ተጠብቆ እንደቆየ ሁሉ በእኛ ትውልድም ተከብሮ ለትውልድ መተላለፍ አለበት ብለዋል ፡፡
አሁን ከፊት ለፊታችን ህልውና የማስከበር ትልቅ ሀላፊነት የሚጠብቀን ወቅት ላይ ስለምንገኝ ፣ ሰንደቅ ዓላማችንን ይዘን የኢትዮጵያን ህልውና አስጠብቀን እናስቀጥላለን ብለዋል ፡፡
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ባህር ሀይል፣ የኢፌዴሪ የልዩ ዘመቻዎች ሀይል እና የመከላከያ ጥናትና ምርምር ማዕከል የሰንደቅ ዓላማ ቀንን አክብረዋል፡፡
በዝግጅቱ የልዩ ዘመቻዎች ሀይል ም/አዛዥ ለሎጂስቲክ ብ/ጄ ታገስ ላምባሞን ጨምሮ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ፣ አባሎች እና የሲቪል አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
በተጨማሪም ቀኑ በምስራቅ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ የተከበረ ሲሆን ÷ የምስራቅ ዕዝ አዛዥ ፅ/ቤት ሃላፊና የኋላ ደጀን አስተባባሪ ኮ/ል ሲሳይ ታደሰ ሰንደቅ ዓላማ ከሰቀሉ በኋላ የሀገራችንን ሉዓላዊነትና የሰንደቃላማችንን ክብር ለመንካትና ለማዋረድ የውስጥ ጠላቶቻችን ከውጭ ጠላቶቻችን ጋር ተዋህደው ጥቃት የከፈቱብን ቢሆንም በሀገራችንና በሉዓላዊነታችን የማንደራደር ኢትዮጵያውያን ግን መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር የተቃጣብንን የተቀናጀ ወረራ መክተን የሀገራችንን ክብር እናስጠብቃለን ብለዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት መላው የኢትዮጵያ የፀጥታ ሃይሎች ለሰንደቅ-ዓላማችን ክብር በዱር በገደሉ እየተዋደቁ ሲሆን÷ በደጀን የሚገኘው የዕዛችን ክፍልም ግንባር ያለውን ሃይላችንን በተፈለገው መንገድ በመደገፍ የተጀመረው የህልውና ዘመቻ በድል እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ በደጀን እግረኛ ክ/ጦር 14ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በድምቀት የተከበረ ሲሆን÷ በክ/ጦሩ መምሪያ በተከናወነው በዚሁ ሰነ-ስርዓት ሰንደቅዓላማ በመሥቀል መልዕክት ያስተላለፉት የደጀን ክ/ጦር አዛዥ ኮ/ል ጌታሁን ካሳዬ ናቸው፡፡
አዛዡ ባስተላለፉት መልዕክት እንደተናገሩት÷ ሠንደቃችንን በደማቸው አስከብረው ዛሬ ላለንበት ከፍታ ያደረሱን ጀግኖች ክብር ይገባቸዋል ካሉ በኋላ ዛሬ በኛ ዘመን ቃላችንን በማደስ ለሀገራችን ሉአላዊነትና ለሠንደቃችን ክብር ማንኛውንም ዋጋ መክፈል ይገባናል ብለዋል፡፡
በዕለቱ የሰንደቅ ዓላማን በተመለከተ የተዘጋጀ መልዕክት የተላለፈ ሲሆን÷ ቃል የመግባት ስነ-ስርዓትም ተከናውኗል፡፡
በተጨማሪም የምዕራብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ የሰራዊት አባላት 14ኛውን ብሄራዊ የሰንደቅ አላማ ቀን ያከበሩ ሲሆን÷ የምዕራብ ዕዝ መሃንዲስ መምሪያ ሀላፊ ኮ/ል ግርማ ወንዳፍራሽ ሰንደቅ ዓላማ የአንድ ሃገር መታወቂያ ፣ የህዝብ አንድነት መጠበቂያና የክብር መለያ ነው ብለዋል፡፡
ሰንደቅ ዓላማችን የድላችን ዓርማ ነው ያሉት መምሪያ ኋላፊው÷ የሀገራችንን ልምላሜ ፣ የወደፊት ተስፋ ፣ ድል አድራጊነትና እኩልነት ለዓለም ያስተዋወቅንበት እንዲሁም አደራ ተቀብለን አደራ የምንሰጥበት የትውልድ ቅብብሎሽ ቃል ኪዳናችን ነው ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ያጋጠመንን የህልውና አደጋ ድል ተነስቶ የሀገርንና የሰንደቅ ዓላማን ክብር በማስቀደም ደማቅ ታሪክ የሚፃፍበት እንደሆነ ገልፀው÷ ሰራዊቱ ለላቀ ግዳጅ እንዲነሳሳ ማሳሰባቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version