አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ባለሙያዎች በሃገር ውስጥ ከሚሰጡት ሙያዊ አገልግሎት በተጨማሪ በአለማቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በመሆን በሃገር ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ አስተዋፆ ሊያደርጉ እንደሚገባ ዶክተር ጀማል አባ ፊጣ ተናገሩ፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ከዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ፋጥማ ኮሌጅ ጋር በህክምና የትምህርት ዘርፍ አብሮ ለመስራት የሚስላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱ ብቁና በአለምአቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ የጤና ባለሙያዎችን በሃገር ውስጥ ማፍራት ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል፡፡
ለዚህም ባለሙያዎች ወደ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ሄደው ልምድ መቅሰማቸውንና ለትምህርትና ስልጠና የሚያገለግሉ ግብዓቶች ከፋጥማ ኮሌጅ መገኘታቸን የጅማ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ኤሊያስ አሊ ተናግረዋል።
የቀድሞው የትምህርት ስርአት÷ ጥራትና ብቃት የሌላቸውን የጤና ባለሙያዎች በብዛት ማምረት ላይ ያተኮረ እንደ ነበር ነው ዳይሬክተሩ የጠቆሙት።
ዛሬ የተደረገው ስምምነት ግን ከሃገር አልፈው በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳድረው መስራት የሚችሉ የጤና ባለሙያዎችን ለማፍራት እንደሚያግዝ ገልፀዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶክተር ጀማል በበኩላቸው፥ ስምምነቱ የጤና ባለሙያዎች በሃገር ውስጥ ከሚሰጡት ሙያዊ አገልግሎት በተጨማሪ ተወዳዳሪ ሆነው በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስና በሌሎች ሃገራት ሰርተው በሃገር ኢኮኖሚ ግምባታ ውስጥ አሻራቸውን እንዲያኖሩ ያግዛል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወክቅትም ብቃት ያላቸው 50 የህክምና ባለሙያዎች የመግቢያ ፈተና ወስደው ወደ ዩናይትድ አረብ ኤምሬስ ሄደው ለመስራት ዝግጅት ላይ ናቸው ያሉት ፕሬዚደንቱ አለማቀፋዊነት የዩኒቨርሲቲው ዋናው መርህ እንደሆነ ገልፀዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን