አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን÷ ምንም እንኳን ኮሪያ በኢኮኖሚ አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ ብትሆንም የሀገሪቷ ባለሥልጣናት ለዜጎች ሕይወት መሻሻል በትኩረት እንዲሠሩ አሳሰቡ፡፡
ኪም ማሳሰቢያውን የሠጡት የሀገሪቷ የላብ አደሮች ፓርቲ 76ኛ ዓመት የምሥረታ ክብረ በዓሉን ባከበረበት ወቅት ነው፡፡
ኪም ÷ የኮሪያ ላብ አደሮች ፓርቲ በ8ኛው ኮንግረስ ላይ ባስቀመጠው የአምስት ዓመታት ዕቅድ መሠረት የሀገሪቷን ኢኮኖሚ ለማሳደግ፣ የአልባሳት፣ የምግብ እና የቤት ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት መሥራት ይጠበቅበታልም ብለዋል፡፡
ኪም አክለውም÷ የአምስት ዓመታት የፈጠራ ሥራ በሀገሪቷ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል፤ ቀጣዩን ታላቅ ፕሮጀክታችንንም በስኬት በመፈፀም እና በማሳየት ኃያል ሶሻሊስት ሀገር እንገነባለን ማለታቸውን ሲጂቲ ኤን ዘግቧል፡፡
በዓለማየሁ ገረመው