የሀገር ውስጥ ዜና

ድርጅቱ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት የኮንቴነርና የከባድ መኪና ግዢዎችን ሊፈጽም ነው

By Meseret Awoke

October 11, 2021

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)በኮሮናና በውስጥ ሰላም እጦት የተዳከመውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት የሚያስችሉ የኮንቴነርና የከባድ መኪናዎችን ግዢ እንደሚፈጽም የኢትዮጵያ ባህር ትራንዚትና ሎጅስቲክ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ፡፡

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ለኢፕድ እንደተናገሩት÷ እንዲገዙ የተፈቀዱት ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ግዢ በኮሮናና በውስጥ ሰላም እጦት ጉዳት የደረሰበትን የኢትዮጵያን የገቢና ወጪ እንቅስቃሴ ለማሳላጥና ቶሎ እንዲያገግም ያስችላል፡፡

በሁሉም ዘርፍ ከውጭ የሚመጡና ከሀገር የሚወጡትን ግብዓቶች በተቀላጠፈ መልኩ ለማጓጓዝም ይረዳል፡፡

በ2014 በጀት ዓመትም የግብርና ምርት ማሳደጊያ የሚሆን የአፈር ማዳበሪያን በማጓጓዝ በኢትዮጵያ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የገለጹት ዋና ሥራ አስፈፃሚው÷ ድርጅቱ በተያዘው የበጀት ዓመት ከአሥር ሚሊየን ቶን በላይ የገቢና ወጪ ጭነቶችን ለማስተናገድ በዕቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡

በ2014 ዓመት የሚጓጓዘው የአፈር ማዳበሪያ ሁለት ሚሊየን ቶን ገደማ ሊደርስ እንደሚችል የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚው÷ ማዳበሪያ በተወሰነለት ጊዜ ግዥው ከተጠናቀቀ ድርጅቱ እንደ አስፈላጊነቱ በመርከብና በከባድ የጭነት ተሽከርካሪ ማጓጓዝ እንደሚጀምር ገልፀዋል፡፡

የማጓጓዝ ሂደቱን በማቀላጠፍም ለአርሶ አደሩ ማህበረሰብ ግብዓቱን በጊዜው እንዲደርስ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!