Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዛሬ ይከበራል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “በአዲስ ምዕራፍ በተሟላ ሉዓላዊነት ለሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ!” በሚል መሪ ቃል 14ኛው የብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን ዛሬ ለ14 ጊዜ ይከበራል፡፡

ሰንደቅ ዓላማ የብሔራዊ አንድነት መገለጫ፤ የአንድ ሀገር ዜጎች ሀገራዊ ፍቅርና ብሔራዊ ስሜትን የሚገልፁበት፤ ታሪካዊ ትስስርና ስነ-ልቦናዊ አንድነት የሚንፀበረቁበት የሀገራዊ አንድነትና ህብረት አርማና ምልክት ነው፡፡

በመሆኑም ብሔራዊ የሰንደቅ አላማ ቀን በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ በመጀመሪያው ሳምንት ሰኞ እንዲከበር በህግ ተደንግጓል፡፡

በዓሉ ዛሬ ከረፋዱ 4፡30 ሠዓት በፌዴራል፣ በክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደር ም/ቤቶች ሰንደቅ ዓላማ በመስቀል እና በሰንደቅ ዓላማ ፊት ቃለ መሐላ በመፈፀም እንዲሁም በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ ይከበራል፡፡

የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል የሚከበረው በአንድ በኩል 6ኛው አገር አቀፍ ብሄራዊ ምርጫ ተካሂዶ በምርጫው ውጤት መሰረትም አዲስ ፓርላማ እና የመንግስት ምስረታ በተካሄደበት ማግስት እና በኢትዮጵያ እውነተኛ ዴሞክራሲ ለመገንባትና ብልፅግናን ለማምጣት አዲስ ምእራፍ በጀመርንበት ወቅት በመሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው የተወካዮች ምክር ቤት አመልክቷል፡፡

በሌላ መልኩ የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችን ብሔራዊ አንድነታችንን እና ሉዓላዊነታችንን እየተፈታተኑ ባሉበት በዚህ ወቅት የሰንደቅ ዓላማ በዓሉን ማክበር፤ ተናበንና ተደራጅተን በተባበረ ክንድ የተጋረጠብንን የህልውና አደጋ ለመመከትና ለመቀልበስ ፤ ለብሔራዊ አንድነታችንና ሉአላዊነታችን ያለንን ቁርጠኝነት በባንዲራችን ፊት ዳግም ቃላችንን የምናድስበት እለት ነውም ብሏል ምክር ቤቱ፡፡

የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት መሪነት በመላው ኢትዮጵያ በፌደራል የመንግስት ተቋማት፣ በክልሎችና በሁለቱም አስተዳደር ከተሞች ፣ የመከላከያ ሰራዊት ካምፖች እንዲሁም በኢምባሲዎችና የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች በተመሳሳይ ሰዓት እንደሚከበር ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version