የሀገር ውስጥ ዜና

የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች ለትምህርት ልማት ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽኦ አበረከቱ

By Alemayehu Geremew

October 10, 2021

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በነቀምቴ የከተማ አስተዳደር ነዋሪው ለትምህርት ልማት ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት አስተዋጽኦ ማበርከቱን የከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ከበደ እንዳስታወቁት የከተማው ነዋሪ በክረምቱ የዜግነት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በጥሬ ገንዘብ፣ በጉልበትና ጥሬ ዕቃን በማቅረብ በ8 ሚሊዮን 406ሺህ 99 ብር የሚገመት አስተዋጽኦ አበርክቷል።

በዚህም እያንዳንዳቸው ሶስትሶስት የመማሪያ ክፍሎች ያላቸው ሰባት ሕንፃዎች፣ 72 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችና 5 መፀዳጃ ቤቶችን በብሎኬት በመገንባት ለአገልግሎት ማዘጋቱን ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ከመማሪያ ክፍሎች ግንባታ በተጓዳኝ የትምህርት ቤቶችን የውስጥ ገቢ ለማሳደግ በከተማው የሚገኙ የኢትዮ-ቴሌኮም ምዕራብ ሪጅን እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ200 እስከ 300 ሺህ ብር በሚገመት ወጪ የአቡካዶ ተክልን ገዝተው በከተማው ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች ማበርከታቸውን አቶ አሸናፊ ጨምረው አመልክተዋል፡፡

የግል ትምህርት ቤቶች ክፍያ ከፍተኛ በመሆኑ ዝቅተኛው ህብረተሰብ ለልጁ መክፈል አለመቻሉን የተናገሩት ኃላፊው የከተማው ሕዝብ ገንዘቡን፣ ጉልበቱንና ጥሬ ሀብቱን በማበርከት በገነባው የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ልጆቹን ለማስተማር እንዲችል ዝግጅት መጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ ሕብረተሰብ በዜግነት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰራው ስራ ትልቅ አርአያ ሊሆን እንደሚችል አንዳንድ የከተማው ነዋሪዎች አስተያየታቸውን ለኢዜአ ሰጥተዋል፡፡

የቡርቃ ጃቶ ክፍለ ከተማ አስተዳዳሪ አቶ መልካሙ ቡልቲ እንዳሉት የክፍለ ከተማው ሕዝብ የመንግሥትን በጀት ሳይጠይቅ በራሱ ተነሳሽነት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 3 የመማሪያ ክፍሎችን በክ/ከተማው ውስጥ አስገንብቶ ለመማር ማስተማሩ ስራ በማዘጋጀቱ ምሥጋና እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡

የቡርቃ ጃቶ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ግርማ ዋቀሳ በበኩላቸው ህዝቡ ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በአጭር ጊዜ ውስጥ 3 ክፍሎች ያሉት የመማሪ ክፍሎችን በብሎኬት ገንብቶ ማዘጋጀቱ ሊበረታታ የሚገባ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቀሶ ክፍለ ከተማ አስተዳዳሪ አቶ ግዛው ሽፈራው በበኩላቸው የክፍለ ከተማው ሕዝብልጆቹን ለማስተማር ባለው ፍላጎት የኑሮ ውድነት ሳይበግረው ግምቱ ከ1ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ አንድ ሕንፃ ገንብቶ ለመማር ማስተማሩ ሥራ ማዘጋጀቱን አመልከተዋል።

የብቂልቱ ሌቃ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የወላጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጥላሁን ሞሲሳ እንዳሉት የትምህርት ቤቱ መምህራን፣ የክፍለ ከተማው አመራር፣ ነዋሪው ሕብረተሰብና ባለ ሀብቱ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት አስገንብተው ለመማሪያ በማዘጋጀታቸው ምስጋና ይገባቸዋል፡፡