አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንደነበረው ሰው አሸባሪው የህወሃት ቡድን የአደገኛ ወንጀለኞች፤ጨቋኞች እና ውሸታሞች ስብስብ መሆኑን አውቃለሁ ሲሉ የቀድሞ የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባል አና ጎሜስ ገለጹ።
አና ጎሜዝ በ1997 ኢትዮጵያ ያካሄደችውን አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ ለመታዘብ የመጣው የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ነበሩ።
በወቅቱ በህወሃት የበላይነት የሚመራው መንግስት ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፤ፍትሃዊ እና ተዓማኒ እንዳይሆን በማድረጉ አና ጎሜዝ ሲያብጠለጥሉት ቆይተዋል።
አና ጎሜዝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚያደርገውን ተደጋጋሚ ጫና በመቃወም ለድርጅቱ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እና ለግብረሰናይ ድርጅት አመራሮች በትዊተር መልዕክት ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በዚሁ መልዕክታቸው በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ እና ልምድ እንደነበረው ሰው የአሸባሪው ህወሃት ቡድን የአደገኛ ወንጀለኞች፤ጨቋኞች እና ውሸታሞች ስብስብ ነው ብለዋል።
የጸጥታው ምክር ቤት እና የሰብዓዊ አቅራቢ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ላይ የሚነዙት ያልተገባ ወቀሳ ነባራዊ ሁኔታን ያላገናዘበ ነው በሚል በርካቶች እየተቃወሙት ይገኛሉ።
በኢትዮጵያ ከተልዕኳቸው ውጪ ሲንቀሳቀሱ ከአገር እንዲወጡ የተደረጉ የተመድ ሰራተኞች ለአሸባሪው ቡድን የተለያየ ድጋፍ ሲያቀርቡ የነበሩ ናቸው።
የአሁኑ ተመድ ኢትዮጵያ ፋሽስቱ የኢጣሊያ መንግስት ጽብ አጫሪነቱን እንዲያቆም እና የሀገሯን ሉዓላዊነት እንዲያከብር ለ’ሊግ ኦፍ ኔሽንስ’ እአአ 1935 ያቀረበችውን አቤቱታ ወደጎን በማለት ለኢጣልያ ይሁንታ መስጠቱ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ አለም አቀፍ ህጎችን መነሻ በማድረግ ለአሸባሪው ቡድን ድጋፍ ያደረጉ የተመድ ተወካዮች ላይ እርምጃ ብትወስድን ፤የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እውነታውን ባለመቀበል ኢትዮጵያ ላይ ፊቱን ማዞሩ ”ታሪክ እራሱን ደገመ ”የሚያስብል አቋም እንዲይዝ አድርጎታል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!