Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ክልሉ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመማሪያና ማስተማሪያ መጻህፍት ላይ ማሻሻያ አደረገ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመማሪያና ማስተማሪያ መጻህፍት ላይ ማሻሻያ ማድረጉን አስታወቀ።

በተደረገው ማሻሻያ ላይ ባለድርሻ አካላት በዛሬው ዕለት ውይይት ያካሄዱ ሲሆን÷ የመጻህፍቱን ሙከራ ደረጃ በዚህ ዓመት በማስተማር ለማስጀመር እንደታሰበም ተገልጿል።

በትምህርት ቢሮው የስርዐተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክተር አቶ ካሴ አባተ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት÷ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት መማሪያ መጻህፍት ላይ መሰረታዊ ማሻሻያዎች ተደርገዋል።

የተደረገው የስርዓተ ትምህርት ማሻሻያ አዲሱን የትምህርት ፍኖተ ካርታ መሰረት ያደረገ ሲሆን÷ ሀገር በቀል እውቀቶችና እውቀት- ተኮር ሀሳቦች እንዲካተቱ እንዲሁም የልዩ ፍላጎትን እና ስርዓተ ፆታን ያማከሉ እንዲሆኑ ተደርጓል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ።

በትምህርት ሚኒስቴር የስርዓተ ትምህርት ጀነራል ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ቴዎድሮስ ሸዋረጋ በውይይቱ ወቅት እንደገለፁት÷ የስርዓተ ትምህርት ቀረፃ ሂደት በመሆኑ በየጊዜው የሚታዩ ክፍተቶችን በማስተካከል በእውቀትና ክህሎት የታነፀ ትውልድ ማፍራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የተሻሻሉት መጻህፍት በዘንድሮ በሙከራ ደረጃ የሚቀርቡ መሆናቸውን የገለፁት ዶክተር ቴዎድሮስ፥ በሂደት የሚጠናቀቀውን የማሻሻያ ስራ ውጤታማ ለማድረም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ያደርጋል ብለዋል።

የክልሉ የትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ማተብ ታፈረ በበኩላቸው ÷ የመጻህፍት ማሻሻያ ዝግጅት በአማራ ክልል ሲካሄድ የመጀመሪያው በመሆኑ ከአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤና ከተመረጡ የመጽሐፍ አዘጋጆች ጋር በትብብር መሰራቱን አብራርተዋ።

በአዲስ መልክ የተሻሻሉት መጽሃፎች ለ2014 የትምህርት ዘመን በሙከራ ደረጃ የሚቀርቡ ሲሆን÷ የስርዓተ ትምህርት ማሻሻያ ተግባሩም ጎን ለጎን ክትትልና ግምገማ እየተደረገበት በቀጣዮቹ ስምንት ወራት የሚጠናቀቅ ይሆናል ተብሏል።

በሙሉጌታ ደሴ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version