Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአስር ዓመቱን “ፍኖተ ብልጽግና” የልማት ዕቅድ ለማሳካት የምክር ቤት አባላት ሚና የጎላ ነው-ዶ/ር ፍጹም አሰፋ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) የአስር ዓመቱን “ፍኖተ ብልጽግና” የልማት ዕቅድ ለማሳካት የምክር ቤት አባላት ሚና የጎላ መሆኑን የፕላን ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ ተናገሩ።
የፕላን ልማት ሚኒስቴር በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ኢትዮጵያ ለማሳካት ያስቀመጠችውን ዕቅድ በሚመለከት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
ከ2013 እስከ 2022 ዓ.ም የሚከናወን የአስር ዓመት “የፍኖተ ብልጽግና” የልማት እቅድ ተዘጋጅቷል።
የፕላን ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ፤ ቀደም ሲል የተከናወኑ የልማት አፈፃጸሞችን፣ አሁናዊ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያና ቀጣይ የሚከናወኑ የልማት እቅዶችን አስፈላጊነትና ዓላማ በሚመለከት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በገለጿቸውም ከ2013 ዓ.ም በፊት በነበሩት አስር አመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአማካይ 9 ነጥብ 2 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን አመላክተዋል።
በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዳስትሪ፣ በኮንስትራክሽንና በአገልግሎት ዘርፍ የተመዘገበውን ስኬት፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና የቀጣይ ዕቅድ ለውይይት መነሻነት አቅርበዋል።
ከ2013 ዓ.ም በፊትም በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሌሎች ዘርፎች ላይ የተሻለ አፈፃጸም ማስመዝገብ ተችሎ እንደነበር አስታውሰዋል።
ነገር ግን ዘገምተኛ ምርታማነት፣ አዝጋሚ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ እድገት፣ የዕዳ ጫና፣ የዋጋ ግሽበት፣ ዝቅተኛ የውጭ ንግድ አፈፃጸም፣ የህግና ተያያዥ የፖሊሲ ተግዳሮቶች ኢትዮጵያ የምትፈልገውን ዕድገት እንዳታስመዘግብ እንቅፋት ፈጥረውባት እንደነበር አመላክተዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን፣ የመዋቅር ክፍተቶችና የክፍላተ-ኢኮኖሚ አዝጋሚነትን ለማስተካከልም የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉን አንስተዋል።
አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ በዕዳ ጫና ቅነሳ፣ በግብርና ምርታማነት በህግና የፖሊሲ ማሻሻያ ላይ ከፍተኛ ለውጥ መመዝገቡን ጠቁመዋል።
የአስር ዓመቱን “ፍኖተ ብልጽግና” የልማት ዕቅድ ለማሳካት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አስፈፃሚውን አካል በመቆጣጠርና በመገምገም የሚኖራቸው ሚና የጎላ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
የምክር ቤቱ የክትትል ስራ ተጠናክሮ የአስፈፃሚው አካል ሃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ከተደረገ የልማት እቅዱ እንደሚሳካም ተናግረዋል።
የአስር ዓመቱ “ፍኖተ ብልጽግና” የልማት ዕቅድ “ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት” የሚያደርግ መሆኑም ተገልጿል።
የምክር ቤት አባላትም የህዝብን አደራ ለመወጣት፤ የኢትዮጵያ የልማት እቅድ እንዲሳካ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የምክር ቤቱ አባላት አገራዊ የልማት እቅዱን በሚመለከት ላነሷቸው ጥያቄዎች ሚኒስትር ምላሽና ማብራሪ መስጠታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው 10 በመቶ እድገት በማስመዝገብ “ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት” ለማድረግ ርዕይ መቀመጡ ይታወቃል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
0
People Reached
0
Engagements
Boost Post
Like
Comment
Share
Exit mobile version