አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጎግል በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የአፍሪካን የኢንተርኔት አገልግሎት ለማሳደግና የአህጉሪቱን ስራ ፈጠራ መስክ ለማነቃቃት 1 ቢልዮን ዶላር ኢንቨስት እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡
ጎጉል ከሳፋሪኮም ጋር በመተባበር ዘመናዊ የአንድሮይድ ስልኮች ወደ አፍሪካ ገበያ ለማስገባት እንደሚሰራም ነው ያስታወቀው።
በአፍሪካ ያለው የኢንተርኔት ተደራሽነት በሚፈለገው ደረጃ ባይሆንም ፤ 50 በመቶ የአህጉሪቱ ህዝቦች ከ18 ዓመት የዕድሜ ክልል በታች የሚገኙ በመሆናቸው የአፍሪካ አህጉር ዋና የገበያ ማዕከል ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡
የጎግል ኃላፊ ሰንድራ ፒቻይ፡ ባለፉት ቅርብ ዓመታት“ግዙፍ እርምጃዎች”ቢታዩም “ እያንዳንዱ አፍሪካዊ በተመጣጣኝ ዋጋ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲያገኝ”መስራት ይጠበቅብናል ማለታቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
ኢንቨስትመንቱ የተሻሻለ ግንኙነትን እና ተደራሽነት እንዲኖር የሚያስችል እንዲሁም ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን የሚያግዝ ነውም ብለዋል ሃለፊው፡፡
ገንዘቡ ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ ደቡብ አፍሪካ ፣ናሚቢያ ፣ ናይጄሪያ እና ሴንት ሄለናን ከአውሮፓ ጋር የሚያገናኘውን የኢኳኖ የከርሰ ምድር ገመድ ጨምሮ ለመሠረተ ልማቶች ግንባታዎች የሚውል እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
ስምምነቱ የ10 ሚሊዮን ወጣት አፍሪካውያንን እና አነስተኛ የንግድ ሥራዎችን በዲጂታል ክህሎቶች ለማሠልጠን ከአራት ዓመት በፊት ጎግል የገባውን ቃል በበለጠ እንዲያሰፋ የሚያስችል ነውም ተብሎለታል፡፡
በአፍሪካ የጎጉል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኒቲን ጋጅሪያ “የአፍሪካ ትልቅ ችግሮች ለመፍታት ከአፍሪካውያን የፈጠራ ባለሙያዎች ውጭ ማንም ሊመጣ አይችልም የሚል ጽኑ እምነት አለኝ” ሲሉ መናገራችውን የዘገበው አል-ዐይን ነው፡፡
ጎጉል፥ ከኬንያው የቢዝነስ አጋሩ ግዙፉ ሳፋሪኮም ጋር በመተባበር ዘመናዊ የአንድሮይድ ስልኮች በመያዝ ወደ አፍሪካ ገበያ ለማስገባት እንደሚሰራም አስታውቋል፡፡
ፕሮጀክቱ በቀጣይ እንደ ኤርቴል፣ ኤምቲኤን፣ ኦሬንጅ እና ቮዳኮም ከመሳሰሉ ኩባንያዎች ጋር እንደሚሰራም ተገልጿል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!