Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በተቋማት አደረጃጀት እና አሰራር ላይ የምክር ቤት አባላት አስተያየት ሰጡ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተቋማት አደረጃጀት እና አሰራር ላይ የምክር ቤት አባላት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት የአስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ ሰላም እና ደህንነትን በተመለከተ የፌዴራል መንግሰት በክልሎች ውስጥ ችግር ሲከሰት በፍጥነት ለምን አይገባም፤ ከክልሎች ጥያቄ እስከሚቀርብለት ድረስ ለምን ይጠብቃል የሚል አስተያየት ቀርቧል፡፡

ለመስኖ ሥራና እና ለአርብቶ አደር አካባቢዎች ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ፣ የከተማ ቤቶችን በሚመለከት በረቂቅ ዐዋጁ ላይ የተጠቀሰ በመሆኑ የገጠር መኖረያ ቤቶችም ሊታከልበት ይገባል የሚሉ አስተያየቶች ቀርበዋል፡፡

የሴቶች ፣ ህጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አደረጃጀት ላይ ‹‹ወጣቶች›› እንዲካተትበት ቢደረግ የሚል አስተያየትም ቀርቧል፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽንን ገለልተኛነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ብሄራዊ ባንክ ለአስፈፃሚው አካል መሆናቸው ቀርቶ ተጠሪነታቸው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሆን የሚል ሃሳብ ቀርቧል፡፡

የመንግስት የሚዲያ ተቋማት ተጠሪነትም አሁን ባሉበት እንዲቀጥሉ በግልጽ መቀመጥ አለበት የሚል አስተያየት ተነስቷል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ወጥ በሆነ መልኩ መደራጀቱ መልካም ሆኖ፣ የቆላማ አከባቢዎች ትኩረት እንዲያገኝም ተጠይቋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥን የሚከታተል ራሱን የቻለ ሚኒስቴር መሥሪያቤት እንዲሆን እንዲሁም፤ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ እንዲሰራ ራሱን ችሎ ቢደራጅ የተሻለ እንደሚሆንም ተጠቁሟል፡፡

በቀረቡት አስተያየቶችና ጥያቄዎች ላይ በተሰጠው አስተያየት፥ አዲሱ አደረጃጀት የተነሱትንና ሌሎች ጉዳዮችን ግምት ውስጥ በማስገባት በየተቋማቱ የስራ መዘርዝር ውስጥ እንዲያካትቱ መደረጉን በመጥቀስ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፥ የሰቶች፣ ህጻናት፣ የወጣቶችና የአረጋውያንን መብት የሚያስጠብቅ እንደሚሆንና ከስያሜ አኳያ በስራ መዘርዝር ውስጥ መካተቱን በመግለጽ ምላሽ ተስጥቷል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ፥ የመስኖ ልማት የአርብቶ አደር አካባቢዎችን በተመሳሳይ በስራ መዘርዝሩ ውስጥ ተካቷል፡፡

አየር መንገድ፤ የመገናኛ ብዙሃን፣ ቴሌና ሌሎች ተቋማት በረቂቅ አዋጁ ያልተካተቱ መሆናቸውንና ራሳቸውን ችለው ሌላ አዋጅ የሚወጣላቸው ይሆናል ተብሏል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version