አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ዛሬ በሚካሂደው 6ኛ ዙር አንደኛ ዓመት አንደኛ ልዩ ስብሰባው የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርንና የሚኒስትሮችን ሹመት ምርምሮ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፥ ዛሬ ከጧቱ 3:30 ጀምሮ የሚካሄደው የም/ቤቱ ልዩ ስብሰባ፥ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ/ም ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ም/ቤቶች የጋራ መደበኛ ስብሰባ ላይ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ የሚቀርበውን የድጋፍ ሞሽን ያደምጣል።
በተጨማሪም የፌዴራል መንግስት የአስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የሚቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ያፀድቃል።
በመጨረሻም የሚኒስትሮችን ሹመት መርምሮ በማጽደቅ የእዕቱን ልዩ ስብሰባ ያጠናቅቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የአስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በቀረበውና በምክር ቤቱ በሚፀድቀው አዋጅ መሠረትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቢኔያቸውን አባላት በእጩነት ለምክር ቤቱ ያቀርባሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባሎችን፥ ከሁለቱ ምክር ቤቶች አባላት ወይም ለሥራው ብቃት አላቸው ብለው ካመኑባቸው ሌሎች ግለሰቦች መካከል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በእጩነት አቅርበው ሹመታቸውን ማጸደቅ እንደሚችሉም የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ያመለክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!