Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሰሜን ጎንደር ዞን ሴቶች በአሸባሪው የትህነግ ቡድን ላይ የጀመሩትን ትግል አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ጎንደር ዞን በጦርነቱ ወቅት የሴቶች አበርክቶን የተመለከተ ውይይት ተደርጓል፡፡
የውይይቱ ትኩረትም በሰሜን ጎንደር ዞን ከአሸባሪው ትህነግ ጋር በነበረው ጦርነት የዞኑ ሴቶች ከፍተኛ መሰዋእትነት ከፍለው አካባቢያቸውን በጠላት ያላስደፈሩና አማራ አንገቱን እንዳይደፋ ያደረጉ በመሆናቸው ጀግንነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡
ውይይቱን ያዘጋጁት የአማራ ክልል ሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ከአማራ ክልል ሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀት ጋር በጋራ በመሆን ነው፡፡
በውይይቱ ላይ የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አውግቸው ሽመልስ ለተወያዮች የመወያያ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡
በጽሑፋቸው በሰሜን ጎንደር ዞን ከአሸባሪው የትህነግ ቡድን ጋር በተደረገው ጦርነት የሴቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ከዚህ በፊት በነበረው ትግል የታዩ ክፍተቶችን እና ጥንካሬዎችን አንስተዋል፡፡
በትግሉ ሴራዎችን በመጎንጎን ልዩነት ለመፍጠር የሚሠሩ አካላት እንደነበሩ በመገንዘብ ይህንም መታገል አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሴቶችና ወጣቶችን ለወታደሩ ደጀን እንዲሆኑ እና ከዚህ በፊት ያሳዩትን የደጀንነት ሥራቸውን እንዲያጠናክሩ መደረግ እንዳለበት ረዳት ፕሮፌሰሩ በጽሑፋቸው አስገንዝበዋል፡፡
በውይይቱም አሸባሪው የትህነግ ቡድን በሰሜን ጎንደር ዞን ወረራ ፈጽሞ የህልውና ዘመቻውን ባስጀመረበት ወቅት የዞኑ ሴቶች የሽብር ቡድኑን ዓላማ በውል ተገንዝበው ዘመቻውን በመቀላቀል በዞኑ ለተገኘው ድል አበርክቷቸው አይተኬ እንደነበር ተነስቷል፡፡
በጦርነቱ ሴቶች ስንቅ ከማዘጋጀት ባለፈ ግንባር ገብተው በመዋጋት ዲሽቃ ማርከው የጣይቱ ልጆች መሆናቸውን በተግባር አስመስክረዋልም ተብሏል፡፡
ዲሽቃና መትረየስ በላያቸው ላይ እያጓራባቸው ቡና አፍልተው ለሠራዊቱ ምሽግ ድረስ በመውሰድ ሠራዊቱን ያጠጡ ሴቶች እንደነበሩም ተጠቅሷል፡፡
ትግሉ ተጀመረ እንጅ አልተጠናቀቀም በመሆኑም የሰሜን ጎንደር ዞን ሴቶች ጀግንነታቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ተብሏል፡፡
ሁሉም የአማራ ክልል ሴቶችና ወጣቶች ልክ እንደ ሰሜን ጎንደር ዞን ሴቶች የአሸባሪውን ትህነግ ዓላማ ተረድተው ትግል ማድረግ እንዳለባቸው በውይይቱ ተገልጿል፡፡
የዞኑ ሴቶችም አሸባሪው የትህነግ ቡድን አሁን ድረስ በወረራ የያዛቸውን ቦታዎች ለማስለቀቅና ትህነግን ታሪክ ለማድረግ የጀመሩትን የጀግንነት ትግል አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ማረጋገጣቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version