አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ወደ አዲሱ የአፍሪካ ህብረት መዋቅር የሚደረግ ሽግግር ግልጽነትን ያረጋገጠ እና የሰራተኞችን መብት ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን እንዳለበት አሳሰቡ።
አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በአፍሪካ ህብረት እየተደረገ ባለው የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ ነው።
በዚህም የአፍሪካ ህብረት የመዋቅር ማሻሻያ የደረሰበትን ደረጀ በተመለከተ በተዘጋጀው ሪፖርት ላይ የህብረቱ አስፈጻሚ ምክር ቤት ውይይት አድርጓል።
በቀረበው ሪፖርት ላይ የአባል አገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አስተያየታቸውንም ሰጥተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በውይይቱ ወቅት የህብረቱ የመዋቅር ማሻሸያ በመሪዎች ጉባኤ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ግቡን እንዲመታ ግልጽነትን ባረጋገጠ እና የሰራተኞችን መብት ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ መከናወን እንደሚገባው ተናግረዋል።
በተጨማሪም የህብረቱ የሰው ሃይል አደረጃጀት መዋቅር ችሎታ እና ሃላፊነት ግምት ውስጥ ያስገባ እንዲሁም ልምድና ብቃትን ማዕከል ያደረገ መሆን እንዳለበት መናገራቸውን ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።