አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ዛሬ በሚካሄደው ታሪካዊ የአዲስ መንግሥት ምስረታና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዓለ ሲመት ሥነ ሥርዓት ላይ የተለያዩ የውጭ አገር መሪዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
በዚሁ መሠረት የሶማሊያ ፣ የጂቡቲ፣ የናይጀሪያና የሴኔጋል ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም ሌሎች የውጭ አገር እንግዶች በኢትዮጵያ አዲስ የመንግስት ምስረታና የጠቅላይ ሚኒስትር በዓለ ሲመት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመገኘት አዲስ አበባ ላይ ታድመዋል።
የሶማሊያ ፕሬዚደንት ሞሐመድ አብዱላሂ ሞሐመድ ( ፋርማጆ)፣ የየጅቡቲው ፕሬዚደንት እስማኤል ኦማር ጊሌህ ፣ የናይጀሪያ ፕሬዚደንት ሙሐመዱ ቡሐሪ፣ የሴኔጋል ፕሬዚደንት ማኪ ሳላ፣ የቀድሞ የናይጀሪያ ፕሬዚደንት ኦሊሴንጎ አባሳንጆ፣ የአልጀሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራማታን ላማምራ፣ የናይጄሪያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጄፍሬይ ኦኒዬማና ሌሎች የውጭ አገር እንግዶች አዲስ አበባ ሲገቡ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በብዙሃኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተመረጠ መንግሥት በሚመሰረትበት ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት አዲስ አበባ ለገቡት የውጭ አገር መሪዎችና ሌሎች እንግዶች ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝተው አቀባበል ያደረጉላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት ናቸው።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው መስራች ጉባኤው፥ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ተወዳድሮ በሕዝብ ውሳኔ አብላጫ ወንበር ያገኘው ብልፅግና ፓርቲ የወከላቸው ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተመርጠዋል፡፡
6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መስራች ጉባኤ፥ አቶ ታገሰ ጫፎን የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ፤ ወይዘሮ ሎሚ በዶን ምክትል አፈ ጉባኤ አድርጎ መርጧል።
በተመሳሳይ 6ኛው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በመስራች ጉባኤው አቶ አገኘሁ ተሻገርን የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ፤ ወ/ሮ ዛህራ ሁመድ አሊን ምክትል አፈ ጉባኤ አድረጎ መርጧል።
በአዲሱ የመንግስት ምስረታና በጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓለ ሲመት ሥነ ሥርዓት ላይ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የፌዴራል መንግስት አመራሮች፣ እንዲሁም አዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፥ ታዋቂ ግለሰቦች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በአሰፋ አሕመድ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!