Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አቶ ታገሰ ጫፎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ሆነው ተመረጡ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መስራች ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎን የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ አድርጎ መርጧል።
አቶ ታገሰ ጫፎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ሆነው በመመረጣቸው የኢትዮጵያን ህዝብ በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።
አቶ ታገሰ ጫፎ ከምክር ቤቱ አባላት 419 ድጋፍና በ6 ድምጸ ተአቅቦ ነው በአብላጫ ድምጽ የተመረጡት።
አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ሰፊ የትምህርትና የሥራ ልምድ ያላቸው ሲሆን፥ በሥነ ህይወት ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ማስተርስ ዲግሪ በዓሳ ሳይንስና እርባታ ከህንድ አገር የማስተርስ ዲግሪ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ከኦፖን ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል።
በሥራ ልምዶቻቸውም ከወረዳ እስከ ዞን አመራርነት ለስምንት ዓመታት፣ የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ የክ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የንግድ፣ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ የክልሉ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ በድምሩ በክልል አመራርነት ለ10 ዓመታት አገልግለዋል።
ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የኢፌዴሪ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ሚኒስትር ዴኤታ በመሆን ሰርተዋል።
የመንግስት የሪፎርም ስራዎች የሥራ ሂደት ለውጥ አመራር በተሻለ ሁኔታ እንዲፈፀም የጎላ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውም ተገልጿል።
በክልሉ የፍት ዘርፍ ስራዎች የመልካም አስተዳደር ፓኬጅ ዝግጅት በተሻለ ደረጃ መምራታቸው በፌዴራል ሥራ የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ጥናቶች በጥልቀት እንዲካሄዱ ማስተባበራቸውና ውጤታማም ማድረጋቸው ተጠቁሟል።
አቶ ታገሰ ጫፎ ላለፉት ሦስት ዓመታት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ሆነው ማገልገላቸው ይተወሳል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version