አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)ዛሬም ሕልውናችንን እና ሉዐላዊነታችንን ከማስከበር የሚቀድም ሆነ የሚበልጥ አጀንዳ የለንም ሲሉ የአማራ ክልል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ መግለጻቸውን ከጽህፈት ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የክልሉ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው እንዳሉት፡-
የአማራ ህዝብ በህልውናው እና በሀገራዊ ሉዐላዊነቱ ላይ ከአሸባሪና ወራሪው የትሕነግ ቡድን የተደቀነበትን አደጋ ለመቀልበስ ፋታ በሌለው ተጋድሎ ላይ ከተጠመደ አስራ አንድ ወራት ተቆጥረዋል፡፡
ዛሬም ቢሆን ከጦርነቱ ቀጥተኛ ጉዳቶች ባሻገር ጦርነቱ ያስከተላቸውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮችን ጭምር ለመቋቋም እልህ አስጨራሽ በሆነ ትንቅንቅ ላይ ይገኛል፡፡
አዲሱ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ቀዳሚና አንገብጋቢ ሥራም ስለ ሕልውናችን እና ሉዐላዊነታችን መከበር ሲባል ተገደን የገባንበትን ፍትሃዊ ጦርነት በዝቅተኛ መስዋእትነት፤ በአጭር ጊዜ በድል አድራጊነት መቋጨት ነው፡፡
የአማራን ህዝብ በሁለንተናዊ ውድቀትና ጉስቁልና ውስጥ ለመድፈቅ እየተንፈራገጠ የሚገኘው አሸባሪው የትህነግ ቡድን የከፈተብንን ወረራ እና ጦርነትን ሣንቀለብስና የክፋት እጆቹ ሳይበጠሱ የክልላችንም ሆነ የሀገራችን ሠላምና ፀጥታ በአስተማማኝ ደረጃ ሊረጋገጥ አይችልም፡፡
ዘላቂ እና ሁለንተናዊ ልማትን ለማረጋገጥ የጀመርነው ጥረትም ይሳካል ብሎ ከማመን ይልቅ ጉምን በእጅ መዝገን ይቀላል፡፡
ሥለሆነም መላው የአማራ ህዝብ እስካሁን ካሳየው አንድነት በላቀ ደረጃ አዲሱ የክልሉ መንግስት ጎን በመሰለፍና ለዘመናት የጎን ውጋት ሆኖ ሲጠዘጥዘው የኖረውን አሸባሪ ቡድን ለመደምሰስ በሚደረገው የመቋጫ ተጋድሎ ላይ የአርበኝነት አሻራውን ሊያኖር ይገባል፡፡
ለአዲሱ የአማራ ክልል መንግስት በብልህና አስተዋይ ልቡና እና በሀገር ወዳድ ጀግኖች አርበኛ አባቶቹ መንገድ ህልውናው የተከበረለት ህዝብ እና ሉዐላዊነቷ የማይደፈር ኢትዮጵያን ከመገንባት የበለጠ አጣዳፊም ሆነ አንገብጋቢ አጀንዳ የለውም፡፡
ምክንያቱም ሕልውናውን ባላስጠበቀ ህዝብ እና ሉዐላዊነቱን ባላስከበረ ሀገር ውስጥ አስተማማኝ ሰላምንም ሆነ ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ አይቻልምና፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!