አዲስ አበባ፣ መሰከረም 23፣2014 (ኤፍ ቢሲ) ባለፈው ዓመት በጣሊያን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ በርካታ ዜጎቿ ከስራ ተፈናቅለው ነበር፡፡
ካባኔ ላሜይም በወረርሽኙ ምክንያት በጣሊያን፣ ሰሜን ቱሪም ውስጥ ከሚገኝ ፋብሪካ ከስራ የተቀነሰ ግለሰብ ነበር፡፡
ላሜይ ÷ በቺቫሶ በሚገኘው የቤተሰቡ መኖሪያ ቤት ከ 3 እህትና ወንድሞቹ ጋር እየኖረ ስራ መፈለግ ጀመረ፡፡
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ነው ላሜይ ቲክ ቶክ ላይ አካውንት ከፍቶ እንደ ጊዜ ማሳለፊያ በማረፊያ ክፍሉ ክሊፖችን እየሰራ መለጠፍ የጀመረው፡፡
የሚለጥፋቸው ክሊፕ ቪዲዮዎችም እንደ አብዛኞች ቲክ ቶከሮች ሁሉ ሲደንስ፣ ቪዲዮ ጌም ሲመለከት፣ የተለያዩ የኮሜዲ ስራዎችን እያስመሰለ ሲሰራ የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን ነበር፡፡
ቀስ በቀስ ላሜይ ፈረንጆቹ “ላይፍ ሀክ” የሚሏቸውን አይነት ቪዲዮዎች በእጆቹ እና በፊቱ አስደናቂ እና ፈገግ የሚያሰኙ አገላለፆች በቀልድ መልኩ እየተቸ በመስራት ይለጥፍ ጀመር፡፡ ይህም እጅግ በጣም ከፍተኛ ተወዳጅነትን በአጭር ጊዜ አስገኘለት፡፡
በአሁኑ ሰዓት ላሜይ ቻርሊ ዲአሚሊዮ ከተባለች በአስራዎቹ የዕድሜ ክልል የምትገኝ ዳንሰኛ ቀጥሎ ቲክ ቶክ ላይ በ114 ሚሊየን ተከታዮች በ2ኛ ደረጃ የሚመራ በአንድ ጊዜ ከስራ አጥነት ወደ ዝነኛነት የተሸጋገረ ግለሰብ ነው፡፡
ላሜይ የ21 ዓመት ወጣት ሲሆን በቲክ ቶክ የተወደደበት ምክንያት በቪዲዮቹ ምንም ቃል ሳይተነፍስ አስገራሚ መልዕክት ማስተላለፍ በመቻሉ ነው፡፡
ምንጭ÷ ሲኤንኤን