አዲስ አበባ፣ መስከረም 22 ፣ 2014 ፣ (ኤፍ.ቢ.ሲ ) ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ የሚከበረው የሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል ባህላዊ ስርዓቱን ጠብቆ በአዲስ አበባ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።
በዓሉን ለማክበር አባገዳዎችንና አደ ሲንቄዎችን ጭምሮ ከተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች የመጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አስቀድመው በከተማዋ የታደሙ ሲሆን፥ የመዲናዋ ነዋሪዎችና ከፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተውጣጡ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎችም በዓሉ በጋራ ወደሚከበርበት ስፍራ በመጉረፍ ላይ መሆናቸውን በየአካባቢው የሚገኙ ዘጋቢዎቻችን መረጃዎችን አድርሰውናል።
አባገዳዎችና አደ ሲንቈዎች፣ ወጣት ሴቶችና ወንዶች ፣ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ታዋቂ ግለሰቦች፣ ፈረሰኞችና አርሶአደሮች ናቸው ባህላዊ ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ በዓሉን ለማክበር የታደሙት።
ውብና ማራኪ በሆኑ ባህላዊ አልባሳትና እሴቶች አሸብርቀው፣ ባህላዊ ጭፈራዎችን እያሳዩና ልዩ ልዩ ዜማዎችን እያዜሙ፤ ፈረስኞችም የተለያዩ ትርኢቶችን እያሳዩ ነው የሰላም፣ የፍቅርና የወንድማማችነት ተምሳሌት የሆነውን የሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓልን እያከበሩ ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ የኢሬቻ በዓልን አስመልክተው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው፣ የኢሬቻ በዓል ፈተናዎችን ተቋቁሞ ወደ ብሩህ ጊዜ በተስፋ የመሻገር በዓል ነው ብለዋል።
የኦሮሞ ህዝብ ፍቅር ፣ ወንድማማችነትና ዕርቅን በሚገነቡ ባህላዊ ዕሴቶች እጅጉን የበለጸገ ህዝብ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ፥ ከኦሮሞ ህዝብ ድንቅ ባህላዊ ዕሴቶች አንዱ የሆነው የኢሬቻ በዓል፥ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ያበረከቱ ቀደምት አባቶቻችን ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች የኢሬቻን መሠረታዊ ዕሴቶች የሚጋሩ በመሆናቸው፥ ኢሬቻ የመላው ኢትዮጵያውያን በዓል መሆኑንም ገልጸዋል።
ከረጅም ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ይከበር እንደነበር የሚነገርለትና የምስጋና፣ የይቅርታ፣ የሰላምና የወንድማማችነት ዕሴቶች መገልጫ የሆነው የሆራ ፊንፊኔ የእሬቻ በዓል፥ ለብዙ ዓመታት ከተቋረጠ በኋላ ከቅርብ ዓመታት ውዲህ ሲከበር የዛሬው ለሦስተኛ ጊዜ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ትናንት ባስተላለፉት መልዕክት፥ በሆራ ፊንፊኔ በሚከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ ለመታደም ወደ ከተማችንና ወደ ከተማችሁ እንኳን በሰላም መጣችሁ፣ እንኳን ለበዓሉ አደረሳችሁ ብለዋል።
የሆራ ፊንፊኔ በዓል በድምቀት እንዲከበር በዓሉ የሚከበርበትን ቦታ በማፅዳት፣ እንግዶችን ተቀብሎ በማስተናገድ፣ ከተማውን በማስዋብ፣ እንዲሁም ሰላምና ፀጥታን በማስከበር ላይ ለተሳተፉ የመዲናዋ ነዋሪዎች እና ተቋማት ፥ ከንቲባ አዳነች ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።
በአሰፋ አህመድ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!