አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)በተለያዩ ምክንያቶች 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሳይካሄድባቸው በቆዩ አካባቢዎች በዛሬው እለት መራጩ ህዝብ የሚወክለውን ለመምረጥ ድምጽ ሰጥቷል።
ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል ምክር ቤቶች ከሚሰጠው ድምጽ በተጨማሪ በደቡብ ክልል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በክልልነት የመደራጀት ጥያቄን ለመመለስ የሚያስችል የህዝቤ ድምጽ ተሰጥቷል።
ይህንኑ አስመልክተው የተለያዩ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን ሰጥተዋል።
ከእነዚህ መካከል ሮይተርስ፣ አልጀዚራ፣ ኤ ኤፍ ፒ፣ ቢቢሲ፣ ፍራንስ 24፣ የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ እና የጀርመን ድምጽ ይገኙበታል።
እነዚህ መገናኛ ብዙሃን ቀደም ሲል ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል ምክር ቤት ምርጫ መካሄዱን በማስታወስ የብልጽግና ፓርቲ ከ436 መቀመጫዎች መካከል 410 መቀመጫዎችን በማግኘት መንግስት መመስረት የሚያስችለውን ድምጽ ማግኘቱን አመልክተዋል።
በዚህም በሚቀጥለው ሳምንት መንግስት እንደሚመሰረት በዘገባቸው ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ሮይተርስ፣ አልጀዚራና ፍራንስ 24 በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ከሚደረገው ምርጫ በተጨማሪ አምስት ዞኖች እና አንድ ወረዳ በጋራ ክልል የመሆን ጥያቄ በማቅረባቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በክልልነት የመደራጀት ጥያቄን ለመመለስ የሚያስችል ህዝበ-ውሳኔ እየተከናወነ መሆኑን በዘገባቸው አካተዋል።
ዘገባቸውም በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት የፌዴራሊዝም ጽንሰ-ሃሳብ የያዘና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት የሚፈቅድ መሆኑን በማንሳት እስካሁን ተግባራዊ ማድረግ ሳይቻል ለረዥም ጊዜ መቆየቱን አመልከተዋል።
ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በህገ መንግስቱ የተደነገገውን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አስነብበዋል።
በዛሬው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት በሶስቱም ክልሎች ሰላማዊ በሆነ መልኩ እየተከናወነ እንደነበረም በየምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘጋቢዎች ከስፍራው ያደረሱት መረጃ ያመለክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!