አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) በልዩ ልዩ ምክንያቶች ምርጫውን በወቅቱ ማከናወን ያልቻሉ ወገኖች ምርጫ ዛሬ ዴሞክራሲያችንን ምሉእ የሚያደርገውን ምርጫ አከናውነዋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ፡፡
ግልጽነትና ተዓማኒነት የታየበት ታሪካዊው ምርጫ በወርሃ ሰኔ ላይ በተከናወነበት ወቅት በልዩ ልዩ ምክንያቶች ምርጫውን በወቅቱ ማከናወን ያልቻሉ ወገኖቻችን፣ ምርጫ ቦርድ በያዘው ተለዋጭ ቀጠሮ መሰረት ዛሬ ዴሞክራሲያችንን ምሉእ የሚያደርገውን ምርጫ አከናውነዋል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ምንም አይነት የጸጥታ ችግር ሳያጋጥም፣ ድምጻቸውን ይበጀኛል ለሚሉት የፖለቲካ እጩ በመስጠት የዜግነት ግዴታቸውን በድል ተወጥተዋል ብለዋል።
በተመሳሳይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚኖሩ የኮንታ፣ የምዕራብ ኦሞ፣ የቤንች ሸኮ፣ የከፋ፣ የዳውሮና የሸካ ሕዝቦች መተዳደር የሚፈልጉበትን የአስተዳደር ክልል በሕዝበ ውሳኔአቸው አሳውቀዋል።
ሁለቱም የዴሞክራሲ ሂደቶች ላይ በነጻነት ፍላጎታቸውን በድምጻቸው መፈጸም ለቻሉ ዜጎቻችንን እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ ብለዋል።
እነዚህ ሰላማዊ የሆኑ የዴሞክራሲ ልምምዶች በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ምርጫ በማስፈጸም ሂደት ውስጥ የተካፈላችሁ አካላት በሙሉ፣ በወንድማማችነት እሴት ላይ ኢትዮጵያዊ መልክ ይዞ እየተገነባ ለሚገኘው ሕብረ ብሔራዊ የዴሞክራሲ ሥርዓታችን መዳበር አሻራችሁን አኑራችኋልና ኢትዮጵያ ታማሰግናችኋለች ሲሉ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!