Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ለኢትዮጵያ ዜጎች ደህንነትና ጥቅም መከበር አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን- ባህሬን

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለኢትዮጵያ ዜጎች ደህንነትና ጥቅም መከበር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የባህሬን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሼክ ናስር ቢን አብዱለራህማን አልካልፋ ገለጹ፡፡
በባህሬን የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት መሪ አምባሳደር ጀማል በከር ከባህሬን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ ሼክ ናስር ቢን አብዱለራህማን አልካልፋ ጋር የኢትዮጵያን ዜጎች ደህንነት፣ መብትና ጥቅም በሚከበርበት ላይ ተወያይተዋል፡፡
የሰራተኞች ደሞዝ ክልከላ፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ኔትወርክ ላይ እርምጃ በሚወሰድበት ሁኔታ እና ህጋዊ መኖሪያ ፈቃድ እያላቸው የሚያዙትን ዜጎች የመብት ጥሰት ጥበቃ በሚያገኙበት አግባብ ላይም መክረዋል፡፡
በውይይታቸውም የባህሬን መንግስት ለኢትዮጵያውያን ያደረገው ድጋፍና እንክብካቤ የሚያስመሰግን መሆኑን አምባሳደር ጀማል ገልጸውላቸዋል፡፡
ያለ መኖሪያ ፈቃድ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከዚህ ቀደም የተሰጠው የምህረት አወጅ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው÷ በወቅቱ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ባለመኖሩ ዜጎቻችን በአግባቡ ያልተጠቀሙ በመሆናቸው በድጋሚ ምህረት እንዲሰጣቸውም አምባሳደሩ ጠይቀዋል፡፡
ሼክ ናስር ቢን አብዱለራህማን አልካልፋ በበኩላቸው÷ በባህሬን ያሉት የኢትዮጵያ ዜጎች ለባህሬን ኢኮኖሚ እያበረከቱ ያሉትን አስተዋጽኦ አድንቀው÷ የተጠቀሱ ችግሮች አልፎ አልፎ መከሰቱን ገልጸዋል፡፡
የዚህ ሁሉ ቁልፍ ችግር ዜጎች መብትና ግዴታቸው እንዲጠበቅ እንዲሁም ችግር ሲደርስባቸው ዝም ማለታቸው ይበልጥ ተጋላጭ እንዲሆን አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የተጠቀሰው የምህረት አዋጅ ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋጋር ምላሽ እንደሚሰጡ አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያን ዜጎች መብትና ግዴታቸውን አውቀው እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ እንዲሁም የሚደርስባቸውን የደህንነት፣ የመብትና የጥቅም ጥሰት አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጻዋል፡፡
ከሁሉም በላይ ዜጎችን ለአደጋ የሚያጋልጡ የሰዎች ዝውውር ኔትወርክ ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ የኢትዮጵያ ዜጎች መብትና ግዴታቸውን አውቀው እንዲንቀሳቃሱ ለማድረግ የጋራ ሴሚናር ለማካሄድ የተስማሙ ሲሆን÷ ችግሮች በሚያጋጥሙበት ወቅት አፋጣኝ የጋራ መፍትሄ እንደሚሰጡ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን በባህሬን ከኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version