Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአሜሪካ እና የታሊባን ስምምነት የአፍጋኒስታንን ውድቀት አፋጥኗል- የአሜሪካ መከላከያ ባለስልጣናት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ ከፍተኛ የመከላከያ ባለሥልጣናት ታሊባን አፍጋኒስታንን በቁጥጥሩ ሥር ማድረጉ በቡድኑ እና በትራምፕ አስተዳደር መካከል በተደረገው ስምምነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ገለጹ፡፡
የዶሃዉ ስምምነት በየካቲት 2020 የተፈረመ ሲሆን÷ አሜሪካ ወታደሮቿን ከአፍጋኒሰታን የምታስወጣበትን ቀንም አስቀምጧል።
ጄኔራል ፍራንክ ማክኬንዚ ስምምነቱ በአፍጋኒስታን መንግስት እና በወታደሮች ላይ አስከፊ ዉጤት እንዲመጣ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
የመከላከያ ሚኒስትሩ ሎይድ ኦስቲን በበኩላቸው÷ ስምምነቱ ታሊባን እንዲጠነክር ረድቷል ብለዋል፡፡
የዶሃዉ ስምምነት የወታደሮችን የመልቀቂያ ቀን ከማስቀመጥ በተጨማሪ እንደ አልቃይዳ ያሉ የሸብር ቡድኖች የአሜሪካን እና የአጋሮቿን ደህንነት አደጋ ላይ እንዳይጥሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ በታሊባን ላይ ሰፊ ግዴታዎችን አስቀምጧል።
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ከተመረጡ በኋላ ወታደሮችን የማስውጣት እቅዳቸዉን ያስቀጠሉ ሲሆን÷ ወታደሮቹ የሚወጡበትን ቀን ግን ከግንቦት ወደ ነሐሴ መጨረሻ እንዲራዘም አድርገዋል፡፡
የአሜሪካ መከላከያ ባለሥልጣናት ይህንን ያሉት ረቡዕ ለተወካዮች ምክር ቤት የመከላከያ አገልግሎት ኮሚቴ ችሎት ላይ ተገኝተዉ ምስክርነት በሰጡበት ወቅት ነው፡፡
ችሎቱ የተካሄደዉ በሺዎች የሚቆጠሩ አፍጋኒስታናዊያን ህይወታቸዉን እንዲታደጉላቸዉ ከተማጸኑና በካቡል አውሮፕላን ማረፊያ ሁከት ከተነሳ ከሳምንታት በኋላ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በወቅቱ በተፈጸመዉ የአጥፍቶ ጠፊዎቹ ጥቃት 182 ሰዎች መገደላቸዉም ተጠቁሟል፡፡
ምንጭ ፡- ቢቢሲ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version