አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጅማ ከተማ በጥቃቅን እና አነስተኛ የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ለተማሪዎች የደብተር እና የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ አበረከቱ፡፡
በኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ጽህፈት ቤት አስተባባሪነት በተዘጋጀው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለአምስት ትምህርት ቤቶች 125 የመማሪያ ወንበሮች የተበረከቱ ሲሆን÷ የመማር ፍላጎት ኖሯዋችው የመማሪያ ቁሳቁስ ማሟላት ላልቻሉ 180 ተማሪዎች የደብተር እና ብዕር ስጦታ ተበርክቷል።
በጅማ ከተማ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን የገለፁት የጅማ ከተማ የኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ ሀይደር ድርብ÷ በዚህ በጎ ተግባር ለተሳተፉ ጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማትን አመስግነዋል።
የጅማ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ እስማኤል ሱሌማን በጅማ ከተማ በመማር ማስተማር የሚረዱ ከ1ሺህ 980 በላይ የትምህርት መርጃ ቁሳቁሶች ከበጎ ፍቃደኞች መሠብሠቡን ገልፀዉ÷ 9 ሺህ የመማሪያ መጽሐፍት መበርከቱንም ተናግረዋል።
የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ቲጃኒ ናስር ጂማ ከተማ ባለፈው ዓመት 1ሚሊየን 100 ሺህ ብር በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከህብረተሰቡ መሰብሰቡን አስታውሰው÷ ለመማር ማስተማር ስራ የሚረዱ የቁሳቁስ ልገሳ ላደረጉ ኢንተፕራይዞችን አመስግነዋል።
ተማሪዎች የተደረገላቸውን የትምህርት ቁሳቁስ በአግባቡ እንዲጠቀሙ እና በትምህርታችው እንዲጎብዙ ለተማሪዎች እና ለወላጆቻቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በወርቅአፈራው ያለው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!