አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሃት በአማራ ክልል በወረራ በገባባቸው አካባቢዎች ያደረሰውን ጥፋት እና ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀላቸውን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ የክልሉ ምክር ቤት አስታወቀ።
ምክር ቤቱ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪውን የህወሓት ቡድን በማውገዝና ለተፈናቀሉት ወገኖች ድጋፍ በማድረግ ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆምም ጥሪ አቅርቧ።
የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ ወርቅሰሙ ማሞ በምክር ቤቱ ስም ባቀረቡት እንዳሉት፣ አሸባሪው ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ ቢፈጽምም ግቡ ኢትዮጵያን መበታተን ነው።
“ይህ አገር የማፍረስ ህልሙ ቢጨናገፍም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች አሁንም ንጹሃን ዜጎችን በመግደል፣ ሃብትና ንብረታቸውን በመዝረፍ እና ሴቶችና ህጻናትን በመድፈር ግፍ እየፈጸመ ይገኛል” ብለዋል።
የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን በማፍረስ፣ በመዝረፍና በማውደም ከእለት ምግብ ጀምሮ የመድሃኒት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃና ሌሎች አገልግሎቶችን ህዝቡ እንዳያገኝ በማድረግ ኢሰብአዊ ድርጊት እየፈጸመ መሆኑንም ነው ያስረዱት።
ችግሩን ለመከላከል ከህግ ማስከበር ጀምሮ አሁንም በህልውና ዘመቻው እየተካሄደ ባለው ጦርነት ክልሉ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት አፈጉባኤዋ ጠቁመው፣ የፌደራል መንግስት ልዩ የበጀት ድጋፍ እንዲያደርግ በምክር ቤቱ ስም ጠይቀዋል።
ወራሪው ቡድን ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀላቸውን በርካታ ንጹሃን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም የሚከናወነው ተግባር በክልሉ በጀት ሊሸፈን እንደማይችልም አመልክተዋል።
ወይዘሮ ወርቅሰሙ አንዳሉት ጦርነቱ መላ ኢትዮጵያዊያንን እንደ ጥንት አባቶች በጀግንነት፣ በቆራጥነትና አልደፈርም ባይነት በአንድነት ገመድ ያስተሳሰረና ያጸና ነው።
“የዓለም መንግስታት፣ ኢምባሲዎች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ጦርነቱ የተጋረጠብንን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ሳንፈልግ ተገደን የገባንበት መሆኑን ሊያውቁልን ይገባል” ብለዋል።
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪውን የህወሓት ቡድን በማውገዝ ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል።
ሽብርተኛው ህወሓት ክልሉን በመውረሩ የተገባበትን ጦርነት ፍትሃዊነት በመገንዘብም ለተጎጂዎች ሰብአዊ እርዳታ ከማድረግ ባለፈ በመልሶ ማቋቋም ሥራው በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
አፈጉባኤዋ ኢትዮጵያዊያን የመከላከያ ሠራዊቱንና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎችን በተለያዩ መንገዶች በመደገፍ ያሳዩትን ቁርጠኝነት ተፈናቃዮችን በመልሶ ማቋቋም ሥራ እንዲደግሙትም አሳስበዋል።
“የአማራ ክልል ህዝብ፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ባለሃብቶች በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ልዩነትን ወደ ጎን በመተው በአንድነት በመቆማችሁ ምስጋና ይገባችኋል” ሲሉ አመስግነዋ “ ልጦርነቱን በድል እንዲጠናቀቅ በገንዘብ፣ በእውቀትና በተለያዩ መንገዶች ያደረጉት ድጋፍ በታሪክ ሲዘከር እንደሚኖር መግለፃቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!