አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የ2014 የኢሬቻ በዓል በፓናል ዉይይት እየተከበረ ነዉ፡፡
ሃገራችን ኢትዮጵያ ለዓለም የምታበረክተው በርካታ ባህል፣ ታሪክና ማንነት አላት ያሉት የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ይታያል ደጀኔ÷ የኦሮሞ ህዝብ ስለ ዕርቅ፣ ሰላምና አንድነት የሚሰብክብት የኢሬቻ በዓል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢሬቻን በዓል ስናከብር የኦሮሞን ባህልና እሴት በጠበቀ መልኩ ሊሆን ይገባል ያሉት የልደታ ክፍለ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ አሸናፊ ብርሃኑ በዓሉን ስናከብር ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር በፍቅር፣ በአንድነትና በመተሳሰብ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
ከተማችን አዲስ አስተዳደር ከሰየመች እና የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ከተካሄደ ማግስት የኢሬቻ በዓል መከበሩ ለየት ይላል ያሉት የአዲስ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አሰፋ ቶላ ናቸዉ።
መስከረም 22 በአዲስ አበባ የሚከበረውን የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በሠላምና በተሳካ ሁኔታ ለማክበር የሚያስችሉ ዝግጅቶች በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ከአመራሩ ጋር ግምገማ መካሄዱን የየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር አስታዉቋል፡፡
ከመላዉ ኦሮሚያ ለሚመጡ እንግዶች አቀባበል ለማድረግ ሙሉ ዝግጅት መደረጉን ከክፍለ ከተሞቹ ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!