አዲስ አበባ፣መስከረም 18፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ)”በመዘግየት የምናጣቸው አሉ፣ በመፍጠን ደግሞ የምናተርፋቸው ስላሉ በአደጋ ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን ለመታደግ ጊዜ የለንም በሚል መንፈስ መድረስ አለብን” ሲሉ ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ ገለጹ።
የፌዴራል እና የአማራ ክልል የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተፈናቃዮችን በፍጥነት ለመደገፍ የሚያስችል አሠራር ላይ ውይይት አድርገዋል።
በውይይታቸውም የአስቸኳይ ጊዜ የአደጋ ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል ፈጣንና ተደራሽ የምግብ ድጋፍ እንዲያቀርብ፣ ከጠላት ነፃ በሆኑ አካባቢዎች ተጎጂዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ መሥራትና በጠላት በተወረሩ አካባቢዎች ላለው ማኅበረሰብ በዓለምአቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አማካኝነት የምግብ አቅርቦት ተደራሽ እንዲሆን የጋራ የትኩረት አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
የድጋፍ አሰጣጡ ሂደት ፍትሐዊና ተደራሽ እንዲሆን መሠራት እንዳለበትም በውይይቱ አጽንኦት ተሰጥቶታል፡፡
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ በቁርጠኝነት ለወገን መሥራት ይኖርብናል ብለዋል።
በተወረሩ አካባቢዎች የሚገኙ ወገኖች በዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ እየተደረገላቸው አለመሆኑንም ተናግረዋል።
ለተፈናቀሉ ወገኖች ሁለንተናዊ ድጋፍ ለመስጠት የተጎጂዎች ፍላጎት በአግባቡ መለየት እንዳለበት ጠቁመዋል።
ከጠላት ነፃ በሚሆኑ አካባቢዎች በአፋጣኝ የዕለት ችግሮቻቸውን የሚፈታ ተግባር መፈጸም እንደሚገባም አስረድተዋል።
ከረጅ ድርጅቶች የሚፈለገው የድጋፍ መጠን በአግባቡ መለየት እንዳለበትም ተናግረዋል። ይህን አስቸጋሪ ወቅት ሁሉም ወገን በመረባረብና በመደጋገፍ ከታሪክ ተወቃሽነት መውጣት ይገባዋል ብለዋል።
ተረጂዎችን በተመለከተ ማንኛውም አካል መረጃ ማግኘት ያለበት ከአስቸኳይ ጊዜ የአደጋ ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል መሆን እንዳለበትም ምክትል ርእሰ መሥተዳደሩ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ፥ አሁን ነፃ በወጡትና ወደፊት ነፃ በሚወጡ አካባቢዎች ዜጎችን ለመርዳት የሚያስችል እቅድ መውጣት አለበት ብለዋል።
በየአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች ተጎጂ ወገኖችን ለመርዳት በወገናዊ ስሜት ርብርብ ማድረግ አለባቸውም ነው ያሉት።
የሚደረገው ድጋፍ ግልጽ በሆነ እቅድ ውስጥ መካተት እንዳለበት አቶ ግዛቸው አስረድተዋል። ለዚህም የተጠናከረና የተዋቀረ የመረጃ ማዕከል ሊኖር እንደሚገባ ነው የጠቆሙት።
እያንዳንዱ መሥሪያ ቤትም ይሁን የሥራ ኀላፊዎች ተጎጂዎችን መርዳት የሚያስችል እቅድ ማውጣት አለባቸው ብለዋል።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትናና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም፥ ተጎጂዎችን በተመለከተ የሁሉም መሥሪያ ቤቶች እቅዶች የጠራ መሆን አለበት ብለዋል።
ተፈናቃዮችን ከመደገፍ አንፃር በየደረጃው የሚገኙ አካላት የሚሠሩትን ተግባር በሚገባ መለየት እንዳለባቸውም አስረድተዋል።
ማን ምን ማቅረብ እንዳለበት መለየትና መታወቅ እንዳለበትም ነው ያሳሰቡት። ሁሉም ዓለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶች የሚደግፉት ድጋፍና መጠን መታወቅ አለበት፤ ተጎጂዎችን በመደገፍ በኩል የጉዳት መጠኑንና አይነትን በመለየት መሠራት አለበት ብለዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ ፥ በክልሉ የሚገኙ ተፈናቃዮች ከዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ የሚፈለገውን ያክል ድጋፍ እያገኙ አይደለም ብለዋል።
ዓለምአቀፍ ሰብዓዊ እርዳታ ድንበር አልባ ቢሆንም ይህን መተግበር ግን አልተቻለም ነው ያሉት። ተጎጂዎችን ለመደገፍ በቂ የሆነና የጠራ እቅድና መረጃ ሊኖር እንደሚገባም መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!