አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)በአዲስ አበባና በአንዳንድ የክልል ከተሞች የታካሚዎች ብዛት በመጨመሩ የጽኑ ሕክምና ክፍል ሞልቶ ታካሚዎች ለከፍተኛ ችግር እየተጋለጡ መሆናቸውን ኢንስቲትዩቱ ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጽጌረዳ ክፍሌ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ አዲሱ የኮቪድ-19 ዝርያ የሆነው ዴልታ ቫይረስ በከፍተኛ ደረጃ እየተሰራጨ በመሆኑ የበርካታ ሰዎች ሕይዎት እያለፈ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በሃገር አቀፍ ደረጃ ከመስከረም 10 እስከ 16 ከተመረመሩት 57ሺህ 940 ሰዎች መካካል 8ሺህ 753 ሰዎች በቫይረስ የተያዙ ሲሆን÷ የመያዝ ምጣኔው ደግሞ 15 በመቶ ነው፡፡
በተመሳሳይ በአንዳንድ ክልሎች የመያዝ ምጣኔ ከሃገር አቀፉ የመያዝ ምጣኔ ከፍ ብሎ መታየቱ የተገለጸ ሲሆን÷ እንደአብነት ሲዳማ 28በመቶ ፣ አማራ 22 በመቶ፣ ኦሮሚያ 22 በመቶ ፣ ደቡብ 24 በመቶ የመያዝ ምጣኔ አስመዝግበዋል፡፡
ይህም የስርጭት መጠኑ ምን ያህል ወደ ክልሎች እየተስፋፋ መሆኑን የሚያሣይ እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡
በተመሳሳይ ሳምንት በሃገር አቀፍ ደረጃ በኮቪድ-19 ምክንያት በአጠቃላይ 271 ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን÷ ይህም ኮቪድ19 በኢትዮጵያ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ የሞት መጠን የተመዘገበበት ሳምንት መሆኑን መረጃው ያሳያል፡፡
በዚህ ሳምንት ከ798 በላይ የሚሆኑ ታካሚዎች ወደ ፅኑ ህክምና ማዕከል ገብተው የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
በአዲስ አበባና በአንዳንድ የክልል ከተሞች የታካሚዎች ብዛት ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ የጽኑ ሕክምና ክፍል ሞልቶ ታካሚዎች ለከፍተኛ ችግር እየተጋለጡ መሆናቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህም አሁን እየታየ ያለው የመያዝ፣ የሞት እና የጽኑ ሕሙማን ቁጥር መጨመር አዲሱ የኮቪድ-19 ዝርያ የሆነው የዴልታ ቫይረስ ስርጭት ከፍተኛ መሆኑ፣ መከላከያ መንገዶች በተገቢው መንገድ ተግባራዊ ያለመደረጋቸው እና የመከላከያ ክትባት ሽፋን ዝቅተኛ መሆኑን እንደ ምክንያት ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በተጨማሪም በህብረተሰቡ ዘንድ መዘናጋት እንዳለ ማንሳታቸውን ከኢንስቲትዩቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!