አዲስ አበባ፣መስከረም 16፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 76ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ያደረጉት ሙሉ ንግግር ÷
ክቡር ፕሬዝደንት፣
ከሁሉ አስቀድሜ የ76ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝዳንት ሆነው በመመረጥዎ እርስዎንና እህት ሀገር ማልዲቭስን እንኩዋን ደስአላችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡
የ75ኛውን ጠቅላላ ጉባኤ ሥራ በብቃት ለመሩት ለክቡር ቮልካን ቦዝኪርም አድናቆቴን እገልጻለሁ።
ከዚህ በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ለማገልገል እጅግ ከፍተኛ በሆነ ድጋፍ በድጋሚ ለተመረጡት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝም እንኳን ደስአሎዎት ለማለት እሻለሁ።
በአለም አቀፍ ደረጃ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስጋት በሆነበት ወቅት ተቀብሎ ላስተናገደን ሀገርም ምስጋና አቀርባለሁ፡፡
ክቡር ፕሬዚዳንት
የዘንድሮው ዓመት የተ.መ.ድ. ጠቅላላ ጉባኤ የCOVID-19 ወረርሽኝን እየታገልን ባለንበት ወቅት የሚካሄድ ሲሆን፤ ወረርሽኙ የሰው ልጆችን ሕይወት ክፉኛ አመሰቃቅሏል። በአንጻሩ ወረርሽኙ ሳይንሳዊ ምርምር እና ፈጠራ የሰው ልጅን ለመታደግ ያላቸውን ግዙፍ አቅምም አሳይቶናል።
በዚህ አጋጣሚ በCOVID-19 ክትባት ምርምርና ግኝት እንዲሁም ስርጭት ላይ ለተሳተፉ ሳይንቲስቶች፣ መሐንዲሶች እና ሌሎች ባለሙያዎች በሙሉ አድናቆቴን እገልጻለሁ።
ሳይንስ ለሰብአዊ አገልግሎት በተገቢው መንገድ ሊውል የሚችለው ፖለቲካ በቀና ልቦና እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ሲመራ መሆኑን አስተውለናል፡፡ በዚህ መሰረት ርትዕን ባልጠበቀ መልኩ በሚደረግ የክትባት ክፍፍል ምክንያት አፍሪካ እጅግ ዝቅተኛ በሆነ የክትባት ተደራሽነት ምጣኔ ከሌሎች የሚተርፉ አነስተኛ የክትባት አቅርቦቶችን ለመጠበቅ ተገዳለች።
ከዚህ ባሻገር በታዳጊ አገራት ላይ ወረርሽኙ እያሳደረ ላለው አስከፊ ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖን ለመመከት በሚያስችል ደረጃ በቂ የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ እርምጃ አልተወሰደም።
ስለሆነም አቅም ያላቸው ሀገሮች የችግሩን ዓለምአቀፋዊ ባህርይና ይዘት ከግምት ያስገባ ትብብርን እንደሚያሳድጉ ተስፋ እያደረግን ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ በዚህ ወረርሽኝ፣ የተናጠል ደህንነት ሊኖር እንደማይችልና የሁላችንም ደህንነት በጋራ ሳይረጋገጥ ማንኛችንም ደህና እንደማንሆን መታወቅ ይኖርበታል፡፡
ክቡር ፕሬዝዳንት፣
የሰው ልጆች እውነተኛ ክብር እና ነፃነት መሰረቱ በዘላቂነት ራሳቸውን መምራት መቻላቸው ነው። የከፋ ድህነት እና የእርዳታ ጥገኝነት ለፖለቲካ፣ ለአስተዳደር፣ ለደህንነት እና ለሰብአዊ ልማት ቀውሶች አባባሽ ምክንያቶች ናቸው።
በሌላ በኩልም የአለም ሙቀት መጨመር ለድህነት መባባስ እጅግ አሳሳቢ እና ገፊ ምክንያት ሲሆን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ኢኮኖሚያቸው በግብርና እና አርብቶ አደር ኢኮኖሚ የተመሰረተ ሀገራት ላይ የህልውና አደጋ ደቅኖባቸዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ምክንያት የምግብ ስርዓታችንን የሚያዛባ የግብርና መሬት መንጠፍና የብዝሃ ሕይወት መመናመን ገጥሞናል። የምንታወቅባቸው የገበያ ሰብሎችን የማምረት ሂደትን የጥራት እና ብዛት ችግሮች አጋጥመውናል። ተከታታይ የጎርፍ እና ድርቅ አደጋ ያለንን ውስን የአስቸኳይ ጊዜ ዝግጁነት ተፈታትነውታል።
የአካባቢ ጥበቃ እና ዘላቂ ልማት ግቦች አፈጻጸም በከፍተኛ ደረጃ የዘገየ በመሆኑ፣ ከአሁን በኋላ ውሱን በሆኑ ኩነቶችና እርምጃዎች ብቻ ሊደገፍ አይችልም። 26ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP 26) የጠፋውን ተፈጥሯዊ ስነምህዳር ለመመለስ ተግባራዊ በመሆን ላይ ላሉት አረንጓዴ ቀበቶ (Green Belt) እና የአረንጓዴ ሌጋሲ የደን ልማት ስራዎች ድጋፍን ለማጠናከር መልካም ዕድል ይፈጥራል የሚል ተስፋ አለን።
ክቡር ፕሬዝዳንት፣
ላለፉት ጥቂት ዓመታት በዚህ መድረክ በሕግ ላይ የተመሠረተ የዓለምአቀፍ ስርዓትና እና የባለብዙወገን ዲፕሎማሲ እንዲጠናከር የቀረቡ ገንቢ ሀሳቦችንና አሳሳቢ ጉዳዮች ሲስተጋቡ ቆይተዋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ለባለብዙ ወገን ተቋማት ያላሳለሰ ድጋፍ ስትሰጥ መቆየቷ የሚታወቅ ሲሆን ይህ ጽኑ አቋማችን የሚመነጨው ከይስሙላ መነሻ ሳይሆን ታሪክ እንደሚመሰክረው ሕግን መሠረት ያደረገ ሥርዓት በችግር ውስጥ በወደቀበት ወቅት ከደረሰብን በደል በመነሳት ነው።
አገራት ወደባለብዙ ወገን ግንኙነት መድረኮች ለመመለስ የሰጧቸውን የቁርጠኝነት ቃሎችን እናደንቃለን። በዚህ ረገድ፣ የአገራት ሉዓላዊነትና እኩልነትን፣ በውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ አለመግባትን፣ እንዲሁም በጋራ ጥቅምና መከባበር ላይ የተመሠረተ ትብብር መርሆዎች አስፈላጊነትን ደግመን ማስታወስ እንፈልጋለን።
የባለብዙ ወገን ግንኙነት ሉዓላዊነትን፣ ውስጣዊ አንድነትን እና የፖለቲካ ነፃነትን ለማስጠበቅ በቆሙ መንግሥታት ትከሻ ላይ የወደቀ መሆኑን እናምናለን። በዚህ ረገድ የባለብዙወገን ግንኙነት ዓላማ ተፈፃሚ የሚሆነው ሃገራት የውስጥ እና የውጭ ጉዳዮቻቸውን በነፃነትና በብቃት ለማስተዳደር ሲችሉ ብቻ ነው፡፡
እርግጥ ነው! የሰው ልጅ የጋራ ፍላጎቶች በመሰረታዊነት ተመሳሳይ እንደሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ነገር ግን በአመለካከት እና በምንከተላቸው ዘዴዎች በባህል፣ በታሪክ እና በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እውነታዎች ውስጥ ባለው ብዝሃነታችን ምክንያት ልዩነት መፈጠሩ የማይቀር ነው።
ብዝሃነትን እንደፀጋ በመውሰድ የውስጥ እና የውጭ ጉዳዮቻችንን በምናስተዳድርባቸው ፖሊሲዎች እና አሰራሮች ላይ ማናችንም በሌላው ላይ የበላይ ሆኖ የመታየት ፍላጎት ሊኖረን አይገባም፡፡
ክቡር ፕሬዝዳንት፣
ከሦስት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ የለውጥ ጉዞ መጀመሯ የሚታወቅ ሲሆን እነዚህ የለውጥ ስራዎቻችን ለዲሞክራሲ፣ ለሰብዓዊ መብቶች፣ ለሰብአዊ ልማት እና ቀጠናዊ መረጋጋት አዲስ የተስፋ ጎህ ቀደዋል፡፡ በብሔራዊ ጥቅምና አካባቢ ሰላም ላይ ጉዳት በማድረስ የተተከለውን ውስብስብ የሙስና መረብ፣ ሕገወጥ ስልጣን፣ እና ሕገወጥ የገንዘብ ፍሰቶችን በማስወገድ ረገድ አበራታች ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡
ይሁንና ለውጡ ከፈተናዎች የፀዳ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ እንደማንኛውም ዴሞክራሲ፣ የዴሞክራሲ ስርዓታችን ግንባታ በመረጋጋት እና በሁከት መካከል ሚዛን ለማስጠበቅ የሚደረግ ሂደት በመሆኑ በእኛ የለውጥ ጥረቶች ውስጥ እኩልነትን እንደ መገፋት የሚቆጥሩ ቡድኖች ሚዛኑን ለማደናቀፍ እና ሁከት ለመፍጠር እንዲሁም የስርዐተ-አልበኝነትን ዕድሜ ለማራዘም የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።
በእነዚህ የጥፋት መሪዎች ተዋናይነት በንጹሃን ዜጎች ላይ ሊገመት የማይቻል ኢሰብአዊ ጥቃት፣ የሁከት ማነሳሳት እና ንብረት ውድመት የደረሰ ሲሆን በመጨረሻም በኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ተፈጽሟል፡፡
ባሳለፍነው ዓመት ጥቅምት 24 ምሽት ምንም አይነት ጥርጣሬ ያልገባቸው የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ከውስጥ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሲሆን ይህን እንደ ሀገር የገጠመንን አደጋ ለመከላከል የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ተገዷል።
ክቡር ፕሬዝዳንት፣
እኛ ይህን የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት ለማሟላት እየተረባረብን ባለንበት ወቅት፣ የጥፋት ቡድኑ የተዘጋጀበትን ሰብዓዊ ቀውስ የመፍጠር እቅድ ተግባራዊ ከማድረጉ በላይ ክፋት የተሞላበት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ተከፍቶብናል፡፡ በግል ፍላጎቶች እና ጥቅሞች የሚዘወር ፖለቲካ እና የውጭ ፖሊሲ ዕውነታውን በመሸፈን የተዛባ የፖሊሲ ውሳኔ ሊያሰጥ እንደሚችልም ተገንዝበናል፡፡
አሁን በደረስንበት ምዕራፍ የሰብአዊ አገልግሎት ድጋፍ የፖለቲካ ዓላማን ማስፈፀሚያ መሳሪያ እንደሆነ እየተገነዘብን መጥተናል፡፡ ወንጀል ጠንሳሾቹና እና ደጋፊዎቻቸው የሃሰት መረጃዎችን በማቀነባበር እንዲሁም ሀሰተኛ ዘግናኝ ምስሎችን በመፈብረክ የተዛባ ግንዛቤ እንዲፈጠር ተንቀሳቅሰዋል፡፡ የህዝባችን እውነተኛ ሰቆቃ በቂ እንዳልሆነ፣ የተወሰነውን የህዝብ ክፍል እንደ አረመኔ ከሚፈርጅ አስተሳሰብ ጋር ለማዛመድ ጥረት የተደረገባቸው ሃሰተኛ ውንጀላዎች ቀርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ ዕርዳታ የመስጠት ግዴታውን መወጣቱ፣ የተናጠል ሰብዓዊ የተኩስ አቁም ማወጁ፣ የምርመራ ሥራዎችን እና ተጠያቂነት የማስፈን እርምጃዎችን መውሰዱ የሐሰት ውንጀላዎችን መቀልበስ አልተቻለም።
በዚህ ሰዓት አጀንዳ በሚቀረፅላቸው እና ቀለብ በሚሰፈርላቸው ሚዲያዎች ተከሰን፣ መርህ አልባ በሆነ ፖለቲካ ተፈርዶብን እንዲሁም በተናጠል የተጣለ ማዕቀብ ተደቅኖብን እንገኛለን፡፡
በቀደሙት ጊዜያት ማእቀቦች በሌሎች ላይ ሲፈፀም መቃወማችን የሚታወስ ሲሆን በተመሳሳይ በኢትዮጵያም ላይ የሚደረግ ፍትህ እና ርቱዕ የሚጎድለው አካሄድ ተግባራዊ እንዳይሆን እንመክራለን፡፡ ምክንያቱም ጫና የሚያሳድሩ ማንኛውም እርምጃዎች ግንኙነቶችን አሻሽለው አያውቁም፡፡
ክቡር ፕሬዝዳንት፣
እኛ የምንወስዳቸው ጥንቃቄ የተሞላባቸው እርምጃዎች ከገጠመን የህልውና ፈተና ጋር ተመጣጣኝ ናቸው። ምንም እንኳን አላስፈላጊ ጫናዎች ቢኖሩብንም፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና የፖለቲካ ነፃነት የማስጠበቅን ከባድ ግዴታ እንወጣለን። ከወዳጆቻችን የሚቀርብልን ትብብር እና ቅን አሳቢነት ተቀባይነት ቢኖረውም ገንቢ አቀራረብን የመጠቀም ፣ መተማመንን የማዳበር እና መረዳትን የመፍጠርን አስፈላጊነት እናሳያለን።
በአንድ ግዛት ውስጣዊ ጉዳይ ላይ ድጋፍን ወይም አልፎ ተርፎም አስተያዬት ለማውጣት የሚደረግ ሙከራ ስለችግሩ ውስብስብነት ሙሉ ግንዛቤን ይጠይቃል። ሊታወቅ የሚገባው ፤ እያጋጠመን ያለው ፈተና በኢትዮጵያ ድንበሮች ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም። መላው የአፍሪካ ቀንድ በዚህ ቡድን የተነደፈለትን አጥፊ መንገድ እየተጋፈጠ ነው። ከዚህ ወንጀለኛ ቡድን ጋር የሚደረገውን ግብግብ ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ መደገፍ የአካባቢያዊ ሰላምን ለማስቀጠል ይረዳል።
ውይይት ሁል ጊዜ የእኛ ተመራጭ የድርጊት አካሄድ ነው። በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ ለሰላም እልህ አስጨራሽ እንቅስቃሴዎች ክፍት ናት። ከዚህ ጋር በተያያዘ ከአፍሪካ ህብረት እና ከአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ጋር ኢትዮጵያ መር ብሔራዊ ውይይት ለመምራት እንሰራለን። ፣ የአፍሪካ ህብረት የራሱን ጥበብ ተግባራዊ ለማድረግ ቦታ ይሰጠዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትን ለማረጋገጥና የአጋሮቻችንን በገለልተኛ ፣ በነጻነት እና በሰባዊነት መርሆች ላይ የተመሰረተ የሥራ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ መንግሥታችን ያላሳለሰ ቁርጠኝነት እንዳለው ለመግለፅ እወዳለሁ። ከዚህ ውጪ በውስጣዊ ጉዳዮቻችን ላይ ጣልቃ ለመግባት የሚቀርብ ማንኛውም ሰበብ ምክንያት አይሆንም ።
አስቀድሞ እንደተደገሰልን የጥፋት ድግስ ቢሆን ኖሮ፤ ኢትዮጵያ ተበጣጥሳ በከሰመች ነበር፡፡ ይህ የስግብግቦች አካሄድ ኢትዮጵያን ብቻ በማፍረስ የሚያበቃ ሳይሆን የአፍሪካ ቀንድን ፖለቲካዊ ምህዳር የሚለውጥና ስትራቴጃዊ ቀጠናውን ወደ የማያባራ ብጥብጥ እና ትርምስ ቀጣና ሊቀይረው ይችል ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ለማንም የደህንነት ስጋት ሆና አታውቅም። ኢትዮጵያ በህዝቦቿ ጽኑ አቋም ሁሌም ሰላም ወዳድ ሀገር ሆና የምትኖርና ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሰላም ወደነበረበት እንዲመለስ የበኩሏን አስተዋፅኦ የምታበረክት ትሆናለች።
ኢትዮጵያ ሀቀኛና ግልጽ ለሆኑ የሰላም እርምጃዎች ምን ጊዜም ዝግጁ ናት፡፡ አፍራሽ ያልሆነ መንገድ ለመከተል ከአፍሪካ ሕብረት እና የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ጋር ትሰራለች፡፡ በዚህም አህጉራዊ ድርጅቱ የራሱን ጥበብ ተጠቅሞ የአህጉሪቷን ችግሮች በራሱ ይፈታል ብለንም ተስፋ እናደርጋለን፡፡
ኢትዮጵያ ሌሎች በተቋሞቻቸው ላይ የደረሱባቸውን ጥቃቶች ሲታደጉ ላበረከተችው ድጋፍና ትብብር ተመሳሳይ ድጋፍ ትሻለች፤ ትጠይቃለችም፡፡
ክቡር ፕሬዝዳንት፣
በአፍሪካ ያለው የፖለቲካ እና የፀጥታ ምህዳር በተለየ ፈታኝ ጉዞ ውስጥ ይገኛል፡፡
መንግስታትን በኃይል መገልበጥ፣ የጋራ ወታደራዊ ልምምዶች፣ ጠበኝነት፣ በሉዓላዊ አገር ውስጥ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት፣ ማፈናቀል እና ቅጥረኝነት፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን መቀራመት፣ ምስጢራዊ ወታደራዊ ስምምነቶች፣ የጂኦ-ፖለቲካዊ ውድድሮች እና ሌሎችም እየተስፋፉ መጥተዋል።
ይህን አካሔድ በፍጥነት መቀየር ካልቻልን አፍሪካን ለማተራመሰና በራሳቸው ሀብት ባይታዋር ለማድረግ እየተካሔዱ ላሉ ጥረቶች አዲስ በር መክፈት ይሆናል ።ከአንድ ወገን ሀይ ባይ የሌለው የበላይነት ይልቅ የብዙ ወገንነትን እና ወንድማማችነትን አርማ ከፍ የሚያደርጉ ብዙ አገራት ይኖራሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
ባለፈው ህዳር ወር ኢትዮጵያ አይታ በማታውቀው የደህንነት ቀውስ ውስጥ በነበረችበት ወቅት ስናምነው የነበረ ጎረቤት አገር የአለምአቀፍ ሕግን በመጣስ ግዛታችንን የወረረ ሲሆን ይህ ወረራ እስከዛሬ ድረስ ቀጥሏል። ኢትዮጵያ ይህንን ችግር ለመፍታት ዲፕሎማሲያዊ የመፍትሔ ሐሳቦችን ለመቀበል ዝግጁ ናት።
አካሄዱን በፍጥነት እስካልቀየርን ድረስ፣ ይህም ሌላው አፍሪካን የማተራመስ እና የአፍሪካውያንን ዕጣ ፈንታ ወደ ከፋ የመብት ጥሰት የሚያሸጋግር ምዕራፍ ይሆናል፡፡ የአንድ ወገን የበላይነት እና ጉልበትን አማራጭ ከሚያደርጉ ሃይሎች ይልቅ የሰላም እና የባለብዙወገን ግንኙነትን ከፍ አድርገው የሚወግኑ ሃገራት በብዛት ይኖራሉ የሚል ዕምነት አለን፡፡
ክቡር ፕሬዝዳንት
ያለፈው ዓመት ለኢትዮጵያ ሕዝብ አዲስ ምዕራፍ የተበሰረበትም ጊዜ ነበር:፡ የዲሞክራሲ ልምምዳችን ወደ አንድ ደረጃ ከፍ ያለበት ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊና ታዓማኒነት ያለው፣ ከፍተኛ የመራጭ ቁጥር የተመዘገበበት ሀገራዊ ምርጫ አካሂደናል፡፡
ሙሉ ለሙሉ በራሳችን ሀብት የገነባነው የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የውሃ ኃይል ማመንጫ የሁለተኛ ዓመት የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ ሌሎችም ሀገራት በራስ አቅም የተነደፈ፣ በራስ ገንዘብ የሚገነባ እና የሚጠናቀቅ የታዳሽ ሀይል ማመንጫዎችን እንዳያለሙ መነቃቃት እንደፈጠረ ይታመናል፡፡
የምኞታችን ተጻጻሪ በመሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ቤቶቻቸው ብርሀን እንዲያገኙ ብሎም ቁጥራቸው እያሻቀበ ለመጣው ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ተስፋ ለመፈንጠቅ የምናደርገው ጥረት በዓለም አቀፍ አካላት የፖለቲካ ትርጉም እየተሰጠው በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት እየተካሄደ ያለውን የድርድር ሂደት ሲያስተጓጉለው ቆይቷል፡፡
ከሁሉም በላይ የሚገርመውና የሚያሳዝነው ነገር ከራሳችን ውሃ እንዳንጠጣ መከልከላችን ነው፡፡ አባይን እና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የእኛ መተማመኛ እውነት፣ ፍትህ እና ጥበብን መሰረት ያደረገው የመተባበር መንገዳችን ነው፡፡
የተፈጥሮ ሃብታችንን የመጠቀም የትውልድ ጉጉት በቅኝ አገዛዝ ውርስ፣ ኢ-ፍትሃዊ በሆነ፣ ሃብትን በብቸኝነት የመቆጣጠር አጉል የተንጠራራ ምኞት አይስተጓጎልም፡፡ የድርድር አጋሮቻችን ይህን በውል ተገንዝበው በአፍሪካ ሕብረት መሪነት በሚካሄደው የድርድር ሂደት ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ውጤት ላይ ለመድረስ እንደሚዘጋጁ ተስፋ እናደርጋለን::
ክቡር ፕሬዝዳንት፤
ንግግሬን በጣም አስፈላጊ በሆነና ሀገሬ በሰላም ማስከበር ረገድ የምትጫወተውን ሚና በማስታወስ መደምደም እወዳለሁ::
በሰላም ማስከበር ዘመቻ ተሰማርተው የሚገኙ ወታደሮቻችን በዳርፉርና በአብዬ የተሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት ተወጥተዋል፡፡ በተ.መ.ድ እና በአፍሪካ ሕብረት በሰማያዊ መለዮ ተሰማርተው ግዳጃቸውን በብቃት ለፈፀሙ የሰላም ማስከበር አባላት አክብሮቴን እና የሕዝባችንን ኩራት ልገልፅላቸው እሻለሁ፡፡
የሰላም ማስከበር ሠራዊታችን ለኑሮ ፈታኝ በሆኑ፣ የእርስ በእርስ የማህበረሰብ ግጭቶች ባሉባቸው፣ መደበኛ ያልሆኑ የጦርነት ዜዴዎች ለሚጠቀሙ፣ የግዛት ባለቤትነት አለመግባባቶች ባሉባቸው ስፍራዎች ተመድበው እንዲሁም ያልተፈቱ አስተዳደራዊ ችግሮችን ተቋቁመው መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በአብዬ የሚገኘው የሰላም አስከባሪ ሀይላችን የሽግግር ሂደት እየተቃረበ ከመሆኑ አንጻር፣ ሁለቱ ጎረቤቶቻችን የግዛት ባለቤትነት ጥያቄያቸው የሚፈታበትን የጋራ ተቀባይነት ያለው ሂደት እና ውጤት ላይ እንዲደርሱ መልካም ምኞታችንን ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡
በመጨረሻም፣ ክቡር ፕሬዝዳንት፣ ለእርስዎ ከፍተኛ ምስጋናዬን እያቀረብኩ፣ የተስፋ ዓመት ሲሉ የሰየሙትን የፕሬዝደንትነት ጊዜዎን በውጤት እንዲፈፅሙ የኢትዮጵያን ሙሉ ድጋፍ አረጋግጥልዎታለሁ።
አመሠግናለሁ።