Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አንድነታችንን አጠናክረን አዲስ የሚመሰረተውን መንግስት ማገዝ ይጠበቅብናል-ሻለቃ አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) የጀመርነውን አንድነት አጠናክረን አዲስ የሚመሰረተውን መንግስት ማገዝ ይጠበቅብናል ሲል አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ ተናገረ።
የሚመሰረተው አዲስ መንግስት ሕዝብ የመምራት ብቃት ያላቸው አመራሮችን ወደ ኃላፊነት ማምጣት እንዳለበትም ገልጿል።
አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ ለኢዜአ እንደተናገረው፥ የሚመሰረተው አዲስ መንግስት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የዕድገት ምዕራፍ በማሸጋገር ረገድ ትልቅ ኃላፊነት አለበት።
ኢትዮጵያን ማሻገር ለመንግስት ብቻ የሚተው ጉዳይ አለመሆኑን ጠቅሶ፥ ኢትዮጵያዊያን የጀመሩትን አንድነት በማጠናከር የሚመሰረተውን መንግስት ማገዝ ይጠበቅባቸዋል ነው ያለው።
ሕዝቡ ምን እና ማን እንደሚበጀው ለይቶ አውቋል ያለው አትሌት ሻለቃ ሃይሌ፥ በመሆኑም ይህን ተገንዝበን እጅ ለእጅ ተያይዘን በመስራት አገራችንን መለወጥ አለብን ብሏል።
መንግስት በበኩሉ እስከታችኛው መዋቅር ሕዝብ የማገልገል ብቃትና ታማኝነት ያላቸውን አመራሮች ወደ ሃላፊነት ማምጣት እንዳለበት ነው የተናገረው።
በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚገቡ አመራሮች ኢትዮጵያ ከገጠሟት ችግሮች እንድትላቀቅ የሚሰሩ መሆን እንዳለባቸውም ጠቁሟል።
ኢትዮጵያን የሚያግዙ ወዳጅ አገሮች እንዳሉ ሁሉ ህልውናዋን የማይፈልጉት አዲስ የሚመሰረተው መንግስት እንዳይጸና የተለያዩ ሴራዎችን ሊያሴሩ እንደሚችሉም ገልጿል።
ነገር ግን ለኢትዮጵያ ህልውና መጠበቅና መልማት ዋነኞቹ ባለጉዳዮች የውጭ ሃይሎች ሳይሆኑ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ተናግሯል።
“ኢትዮጵያ የከፍታ ጉዞዋን ጀምራለች” ያለው ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ፥ የከፍታ ጉዞ ሲጀመር ፈተናዎች ማጋጠማቸው የሚጠበቅ ጉዳይ ነው ብሏል።
በመሆኑም ፈተናዎችን በመጋፈጥ ኢትዮጵያን ከከፍታው አናት ላይ ማስቀመጥ እንደሚገባ አመልክቷል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version