የሀገር ውስጥ ዜና

በጎንደር ከተማ ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎችና አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት እውቅና ተሰጠ

By Meseret Awoke

September 25, 2021

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)በጎንደር ከተማ ባለፈው የትምህርት ዘመን ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች እና ለትምህርት ስራው ውጤታማነት አስተዋፅኦ ላደረጉ ባለድርሻዎች እውቅና ተሰጠ።

የጎንደር ከተማ ከንቲባ ሞላ መልካሙ እንደተናገሩት ዓመቱ በኮሮና ቫይረስና በህግ ማስከበር ዘመቻው የተነሳ ፈተናዎች የነበሩበት ቢሆንም ተማሪዎች ጥሩ ውጤት ማምጣት ችለዋል ብለዋል።

ከተማዋ ውስጥ ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች ይህንን ሽልማት ያበረከትነው ያለፉት ፈተና ቀላል ስላልነበረ ነው ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ አክሊሉ ወንድምአገኘ ዓመቱ በፈተናዎች የተሞላ የነበረ ቢሆንም ከ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ውስጥ 14ቱ ከ600 በላይ በማምጣት ከፍተኛ ውጤት አምጥተዋል ብለዋል።

የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተናን ከወሰዱት ውስጥም 97ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑት ወደ ቀጣዩ ክፍል ማለፍ መቻላቸው በስኬት የሚታይ ነው ብለዋል።

ይህንን በማስመልከት ከ5ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ብልጫ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ስለመስጠታቸውም ተናግረዋል። ለትምህርት ስራው ውጤታማነት አስተዋፅኦ ላደረጉ ባለድርሻዎችም እውቅና ተሰጥቷል።

ከዚህ በተጨማሪም የጎንደር ከተማ አስተዳደር በህልውና ዘመቻው ሰማዕት ለሆኑ ጀግኖች ቤተሰብ ልጆች በ2014 የትምህርት ዘመን ሙሉ የትምህርት ወጪያቸውን በመሸፈን ለማስተማር መዘጋጀቱንም አስታውቋል።

ከተማ አስተዳደሩ በ2013 የትምህርት ዘመን ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች እውቅና በመስጠት የ2014 የትምህርት አጀማመር ንቅናቄ መድረክ አካሄዷል።

የከተማው ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ በመድረኩ እንዳሉት÷ ለሀገራቸው ክብርና ለህዝባቸው ህልውና ሰማዕት የሆኑ ጀግኖችን በማሰብ ልጆቻቸውንና ቤተሰቦቻቸው የከተማ አስተዳደሩ በሚችለው አቅም ሁሉ ይደግፋል።

ለሃገራቸውና ህዝባቸው ሲዋደቁ የተሰዉ የሰማዕታት ልጆች ትምህርታቸውን የሚከታተሉትም 81 የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንደሆነ ገልፀዋል።

“የከተማ አስተዳደሩ የተማሪዎቹን የትምህርት ቁሳቁስ፣ ዩኒፎርምና የትምህርት ቤት የክፍያ ወጪያቸውን በመሸፈን መደበኛ ትምህርታቸውን ተከታትለው ውጤታማ እንዲሆኑ የቅርብ ክትትል ይደረጋል”ብለዋል።

በተጨማሪም በህወሃት የሽብር ቡድን ወረራ ሳቢያ በአጎራባች ዞኖች የተፈናቀሉ ተማሪዎችን በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጅት መደረጉንም አስታውቀዋል።

በ2013 የትምህርት ዘመን በከተማው የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከ100ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስተናገድ የመማር ማስተማር ስራውን በስኬት ማጠናቀቅ መቻሉን የገለጹት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ አክሊሉ ወንድማገኝ ናቸው።

ከህዝቡ፣ ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች በተገኘ 70 ሚሊየን ብር ወጭ የትምህርት ቤቶችን ገጽታ ለማሻሻል የሚያግዙ የ110 መማሪያ ክፍሎች ግንባታና የትምህርት ቁሳቁሶች ማሟላት ስራ መከናወኑንም ገልጸዋል።

መምሪያው በ2014 የትምህርት ዘመን ከ120 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ማቀዱን ጠቅሰው÷ ከደረጃ በታች የሆኑ 29 ትምህርት ቤቶችን ገጽታ ለመቀየር የሚያስችሉ የግንባታና የጥገና ሰራ እንደሚካሄድም አስረድተዋል።

በንቅናቄ መድረኩ ከ5ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ባሉ የትምህርት ደረጃዎች አንደኛ ለውጡ 240 ተማሪዎች ሜዳሊያና የምስክር ወረቀት ሽልማት ተበርክቷል።

በ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ከ600 በላይ ውጤት ላመጡ 14 ተማሪዎች የታብሌትና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል።

በትምህርት ዘመኑ ለመማር ማስተማር ስራው መሳካት ግንባር ቀደም አስተዋጽኦ ለነበራቸው መምህራን፣ የትምህርት ባለሙያዎችና ተቋማት የእውቅና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።

በነብዩ ዩሃንስ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!